ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአበርገሌ ከ47 በላይ ሰዎች በመድኃኒት እጥረት መሞታቸውን ነዋሪዎች እና ባለሥልጣን ተናገሩ
በህወሓት ኃይሎች ተይዞ እንደቆየ በተገለጸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ በሚገኘው አበርገሌ ወረዳ በመድኃኒት እና በምግብ እጥረት የ47 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው አስተዳዳሪ እና ቤተሰቦቻቸውን በሞት ያጡ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
አስተዳዳሪው አቶ አለሙ ክፍሌ ከሁለት ዓመታት በላይ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር የቆየው ወረዳው፣ ረቡዕ መጋቢት 20/2015 ዓ.ም. መለቀቁን ገልጸው፣ የመከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሥፍራው መግባታቸውን ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ አደረኩት ባሉት ማጣራት እና ቀድሞ በነበራቸው መረጃ መሠረት ከ47 በላይ ሰዎች በመድኃኒት፣ ሕክምናና በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።
ኪሮስ ገላው የተባሉ የወረዳው ነዋሪም የወንድማቸውን ባለቤት በወሊድ ምክንያት በሞት ማጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሙሉነሽ ጣፈጠ ሲሉ የሚጠሯት እናት፣ ሦስተኛ ልጇን ለመውለድ ለቀናት ካማጠች በኋላ በስቃይ ብትወልድም ከወሊድ በኋላ ባጋጠማት የደም መፍሰስ የሕክምና እርዳታ ሳታገኝ ሕይወቷ ማለፉን አቶ ኪሮስ ተናግረዋል።
“ለአምስት ቀናት አምጣ ወለደች። ከዚያ የደም መፍሰስ አጋጠማት የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ በቃሬዛ ተሸክመን በእግር ወደ ሰቆጣ ለመሄድ ጉዞ ጀመርን። [ከአበርገሌ ሰቆጣ በእግር አንድ ቀን ይወስዳል] ነገር ግን መንገድ ላይ ሞተችብን” ብለዋል።
ሙሉነሽ 7 እና 9 ዓመት የሚሆናቸው ልጆች እናት የነበረች ሲሆን፣ አዲስ የተወለደው ሕጻንም በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አቶ ኪሮስ ተናግረዋል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ “ሲቪል ነበሩ ያሏቸው” የ16 እና የ22 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሁለት ልጆቻቸው እንደተገደሉባቸውም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ ዞን ውስጥ የሚገኙት የአበርገሌ እና ጻግብጅ ወረዳዎች የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደነበር ነዋሪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ሲገልጹ ነበር።
በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በሰቆጣ ከተማ ያለበቂ ድጋፍ በችግር ውስጥ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ በወቅቱ በህወሓት ሥር ናቸው ስለተባሉት አካባቢዎች እና በስፍራው ስላለው ሰብአዊ ቀውስ ለማወቅ ቢቢሲ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑትን ክንደያ ገ/ሕይወትን (ፕሮፌ.) ጠይቆ፣ በአካባቢው በቡድናቸው ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ቦታ የለም ማለታቸው ይታወሳል።
የወረዳው አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አለሙ ትግራይ ኃይሎች ያለምንም የፀጥታ ችግር አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን ገልጸው፣ የወረዳው ባለሥልጣናት ወደ አካባቢው ገብተው ሕዝቡን ማነጋገር መቻላቸውንም ገልጸዋል።
“ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት እና አገልግሎት የሌለበት፣ የመድኃኒት እጦት ያለበት፣ ምንም ዓይነት ተቋም አገልግሎት የማይሰጥበት ወረዳ ነው ያገኘነው” ብለዋል።
ያለምንም መሠረተ ልማት ከተቀረው አካባቢ ጋር ተቆራርጦ በቆየው ወረዳው ውስጥ የቆዩ ነዋሪዎችም በከፍተኛ ችግር ላይ መቆየታቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በዚህም አበርገሌ ከሚባለው ቀበሌ ብቻ ከ47 በላይ ሰዎች በመድኃኒት እጥረት እና በተለያዩ ችግሮች ሕይወታቸው ማለፉን አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወሊድ ምክንያት የሞቱ እናቶች መኖራቸውንም አክለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት አሁንም በመድሃኒት እጥርት፣ በወባ በሽታ የሚሰቃዩ እና ምንም ዓይነት የጤና አገልግሎት ያላገኙ ሰዎች አሉ።
በእርሻ እና በእንስሳት እርባታ የሚተዳደሩትና የሰባት ልጆች አባት እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ኪሮስ በበኩላቸው፣ “በወረዳው ሁሉም ችግር ላይ ነበር። በረሃብ የሞተም አለ። መንግሥት ከገባ በኋላ መፍትሔ ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
አቶ አለሙ የመንግሥት ኃይሎች አሁን ወደ ሥፍራው መግባታቸውን ተከትሎ “መድኃኒት እና የውሃ ማጣሪያዎችን እንዲሁም ምግብ ነክ እርዳታ ለማድረስ እየሰራን ነው” ብለዋል።
ተፈናቅለው የነበሩ ነዋሪዎችንም ወደ ቀያቸው ለመመለስ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
በአበርገሌ ወረዳ ከ80 ሺህ በላይ ሕዝቦች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ወደ 37 ሺህ የሚሆኑት ተፈናቅለው በዞኑ ዋና ከተማ ሰቆጣ ተጠልለው እንደሚገኙ ኃላፊው አክለዋል።
ከአንድ ወር በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዞኑ አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ ወ/ሮ ዝናሽ ወርቁ በዞኑ ብቻ ከ67 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ እና በቂ ድጋፍ እያገኙ እንዳልሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።