ለረጅም ዓመታት ሲራዘም የቆየው የደቡብ ሱዳን የመጀመሪያው ምርጫ ሊካሄድ ነው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በተለያዩ ጊዜያት ቀን ሲቆረጥለት የቆየው እና ደቡብ ሱዳን አገር ሆና ከተመሠረተች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታካሂደው ምርጫ በቀጣይ ዓመት ታኅሣሥ ላይ እንደሚደረግ የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ከዓለም አገራት በዕድሜ ትንሿ የሆነችው የደቡብ ሱዳን መሪዎች፤ አገሪቱ ነጻነቷን ካወጀችበት ከአውሮፓውያኑ 2011 ወዲህ ለምርጫ ቀርበው አያውቁም። ፕሬዝዳንቱ ሳልቫ ኪርም በመንበሩ ላይ ለ15 ዓመታት ቆይተዋል።

በዋናው ዕቅድ መሠረት የአገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ መካሄድ የነበረበት ከ11 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2015 ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ተራዝሟል።

በ2018 ላይ የሰላም ስምምነት ሲፈረም የአንድነት መንግሥቱን ኪር እንዲመሩት፤ ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር ደግሞ ምክትላቸው እንዲሆኑ ተደርጓል። የሰላም ስምምነቱ 2022 ላይ ምርጫ እንዲካሄድ ያለመ ቢሆንም በአገሪቱ መሪዎች መካከል በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት ሳይደረግ ቀርቷል።

አሁንም ቢሆን በሁለቱ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ምርጫው በድጋሚ እንዲራዘም ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ባለፈው ዓመት ሪክ ማቻር ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸው ተነስተው በቁጥጥር ስር ውለዋል። በግድያ፣ የአገር ክህደት እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ክስ ተመርሥቶባቸዋል። ማቻር የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች ውድቅ አድርገዋል።

አሁን በዋና ከተማዋ ጁባ ውስጥ በቁም እስራ ላይ ያሉ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት መጋቢት አንስቶም በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት እየተካሄደ ነው።

የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ወደ ሙሉ የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስገባ የሚችል ግጭት በድጋሚ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

የአገሪቱ የምርጫ ኃላፊ አቤድኔጎ አኮክ ካቹል ምርጫው ታኅሣሥ 13/2019 ዓ.ም. እንደሚካሄድ አሳውቀዋል። ኃላፊው፤ ያልተፈቱ የሕግ ማሻሻያ ጉዳዮች እና የበጀት እጥረት የምርጫ ዝግጅቱ ላይ እንቅፋት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ አልሸሸጉም።

"የፖለቲካ ቁርጠኝነቱ የእኛ [ኃላፊነት] አይደለም፤ የሚወደቀው መንግሥት ላይ ነው" ብለዋል።

በሚቀጥሉት ስድስት ወር ውስጥ በጀት የማይገኝ ከሆነ ምን እንደሚፈጠር የተጠየቁት ካቹል፤ ኮሚሽናቸው "እውነታውን ያገናዘበ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ" እንዲኖር ማስተካከያዎችን እያደረገ ማቀዱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ኪር ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ በአውሮፓውያኑ 2018 የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለመተግበር እና ደቡብ ሱዳንን በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጎዳና ላይ ለማቆየት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ በፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ምክክር እየተዘጋጀ እንደሆነ ተነግሯል። ይህ ምክክር በፖለቲካ ባለድርሻ አካላት መከካል ስምምነት ለመፍጠር እንደሚረዳም ተገልጿል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ግን የደኅንነት ሁኔታዎች፣ የፖለቲካ ነጻነት እና የምርጫ ዝግጁነትን በተመለከተ ስጋታቸውን አንስተዋል።

'ሳውዝ ሱዳንስ ፒፕል ሊበሬሽን ሙቭመንት ኢን ኦፖዚሽን' (SPLM-IO) የተባለው የሪክ ማቻር ፓርቲ፤ ምርጫ አሁንምም "አደገኛ" ጉዳይ መሆኑን በመግልጽ ተሳታፊዎችን አስጠንቅቋል።

"በታላቁ ኤስፒኤልኤም-አይኦ ቁጥጥር ስር ባሉ ግዛቶች ውስጥ ለመራጮች ምዝገባ እና ለቅስቀሳ የሚመጣ ማንኛውም ሰው የጦር እስረኛ ይሆናል" ሲሉ የፓርቲው ጊዜያዊ ሊቀ መንበር በፌስቡክ ገጻቸው አስጠንቅቀዋል።

"አስታውሱ፤ አገሪቱ ጦርነት ላይ ነች" ብለዋል።