ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአላማጣ ከተማ ወቅታዊ ሁኔታ እና የነዋሪዎች ቅሬታ
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባናል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ለሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአማራ ክልል ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት የተለያዩ ሃሳቦችን ያንጸባርቃሉ። በአላማጣ ከተማ እና በአካባቢዋ ያሉ የትግራይ ተወላጆች እየደረሰባቸው ያሉ “ግፎች አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን” ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ አካባቢው በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከመግባቱ በፊት የቀድሞ የከተማዋ ከንቲባ እየቀረቡ ስላሉ ክሶች እና በአሁኑ ወቅት የአላማጣ ከተማ ከንቲባም ለሚቀርቡት ክሶች ምላሽ ሰጥተዋል።
የነዋሪዎች ስጋት
የአላማጣ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ንግስት (ስሟ ለደህንነት ሲባል ተቀይሯል) “ትግርኛ ተናጋሪዎች ተወልደን በኖርንበት አካባቢ የግፍ እና የማስፈራራት ሰለባ ሆነናል” በማለት አሁን ያሉበት ሕይወት በፍርሃት እና ስጋት የተከበበ “የጨለማ ህይወት ነው” ትላለች።
ሌላ ስሙ እንዲጠቀስ ያለፈለገ የከተማዋ ነዋሪ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው የአካባቢው ተወላጆችም ጭምር የሚገኙበት የከተማዋ አስተዳዳሪዎች “የጁንታ አባል ነህ” በሚል በነዋሪዎች ላይ ግፍ እና እስራት እየፈጸሙ ነው ይላል።
አክሎም በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ውስጥ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸውን በመግለጽ “አማራ ነን እንድንል እየተገደድን ነው” ብሏል።
ነዋሪዎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ ወይም መናገር እንደማይችሉ በመግለፅ በከተማዋ እንደፍላጎታቸው መኖር እና እንደ እርዳታ ያሉ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉት የተሿሚዎቹ እና የታጣቂዎቹ የቅርብ ሰዎች ወይም ናቸው ይላሉ።
የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎች እንግልት እያጋጠመን ነው የሚሉባት ከተማ አላማጣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስር፣ በሰሜን ወሎ ዞን እንደምትገኝ የከተማዋ ከንቲባ ኃይሌ አበራ ለቢቢሲ ትግርኛ አረጋግጠዋል።
“በአሁኑ ወቅት ከተማችን በጣም የተረጋጋች እና ሰላማዊ ነች” የሚሉት ከንቲባው ሕገ መንግሥታዊ እልባት እስኪደረግበት ድረስ በአማራ ክልል ስር እንደምትቀጥል እና “የአማራ ክልል መንግሥትም ለተለያዩ ፕሮጀክቶች በጀት እየላክልን ነው” ብለዋል።
“እንግልት እና በደል”
የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የፖሊስ አባላት በከተማዋ ተሰማርተዋል። የፋኖ ታጣቂዎችም ከከተማዋ ውጭ ዳርዳሩን ይገኛሉ።
ነዋሪዎቹ በተለይ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በከተማዋ እና አካባቢዋ ተሰማርተው ባሉበት ሁኔታ በፋኖ ታጣቂዎች እና የአማራ ልዩ ሃይል አባላት ሰቆቃ እና ግፍ ሲደርስባቸው በማየታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
በከተማዋ የትግራይ ተወላጆች የተለያዩ በደሎች እንደሚደርስባቸው የምትናገረው ንግሥት “አላማቸው ትግራዋይ የሚባል በከተማዋ እንዳይኖር ማድረግ ነው” ትላለች በምሬት።
ከዚህም በተጨማሪም ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከመቀለ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ የሚያልፉ መንገደኞች ሳይቀሩ በማንነታቸው ምክንያት ለእንግልት እና እስራት እንሚጋለጡ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
በከተማዋ ውስጥ “ፋኖ የሚባል ታጠቀ ቡድን የለም” የሚሉት ከንቲባው አቶ ኃይሉ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች በከተማው አስተዳደር ስር ሆነው ፀጥታ ለማስከበር ተሰማርተው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“ጦርነት በተካሄደበት አካባቢ ምንም ክፍተት አይኖርም ማለት አይቻልም። የተባለውን ድርጊት እየፈጸሙ ያሉ አካላት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ የደንብ ልብስ የለበሱ ሕገወጥ ሰዎች መሆናቸውን ደርሰንበታል። እርምጃም እየወሰድን ነው” ብለዋል።
በተደረገ ፍተሻም ሰዎቹ ወታደራዊ ዩኒፎርም የሚለብሱበት ቦታ እንደተገኘ ከንቲባው ጨምረው ገልፀዋል።
ተፈናቃዩ ከንቲባ
አቶ የማነ ከ2007 ጀምሮ በተለያዩ ሹመቶች እና የመንግሥት ኃላፊነቶች በአላማጣ ከተማዋ ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።
የከተማዋ ከንቲባ የሆኑት በመጋቢት 2014 እንደሆነ የሚገልጹት የቀድሞው ከንቲባ፣ በአሁኑ ጊዜ ግን የአማራ ታጣቂዎች ከተማዋን በመቆጣጠራቸው ተፈናቅለው ከከተማዋ ለመውጣት እንደተገደደ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
በከተማዋ ያሉ ታጠቂ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ የተለያዩ አይነት በደሎችን እንደሚፈጽሙ የሚገልጹት የቀድሞው ከንቲባ፣ “የአካባቢውን የሥነ ሕዝብ አወቃቀር መለወጥ፣ ግድያ እና መሰወር፣ ንብረት መዝረፍ እና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን እየፈጸሙ ነው” ሲልም ይከሳሉ።
በነዋሪዎች ላይ በሚደርሰው ግፍ እና በደሎችም የአማራ ክልል ታጣቂዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ የከተማው ተወላጆችም እጃቸው እንዳለበት የቀድሞ ከንቲባው እናገራሉ።
“የከተማዋ አስተዳደር መዋቅር የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው መልኩ ነው እየሄደ ያለው። በጀትም እየቀረበ ያለው በአማራ ክልል መንግሥት ነው። በአጠቃላይ የአስተዳደሩ አደረጃጀት የክልሉን መንግሥት ተልዕኮ የያዘ ነው” ብለዋል።
የነዋሪዎች መታወቂያ ለውጥ
ንግስት እና ሌላኛው ነዋሪ “ማንነታችንን እንድንቀይር እና በኃይል አማራ መሆናችንን እንድናምን እየተገደድን ነው” ሲሉ ስላለው ሁኔታ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
የቀድሞ ከንቲባ አቶ የማነ እና የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶች በአማርኛ ለማስተማር እየተገደዱ ሲሆን፣ በትግርኛ የተዘጋጁ መጽሐፎችም ከአማራ ክልል በተላኩ የአማርኛ መጽሐፎች እየተተኩ ይገኛሉ።
“በየጊዜው ሰልፍ እየጠሩ ‘አማራ ነን’ እንድንል እንገደዳለን” የምትለው ንግሥት የንግድ ቤቶች ስምም ከትግርኛ ወደ አማርኛ እንዲቀይሩ እየተገደዱ ነው ትላለች።
ሌላኛው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገረው በአሁኑ ወቅት የነዋሪዎች መታወቂያ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ወደ አማራ ክልላዊ መንግስት እየተቀየረ ነው።
“የመታወቂያ ካርዱ ‘በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር’ በሚል ነው እየተተካ ያለው። እያንዳንዱ ነዋሪ አዲሱን መታወቂያ እንዲይዝ ይገደዳል” በማለትም ሁኔታውን ይገልፃል።
ነባሩ መታወቂያ በአዲሱ በሚተካበት ሂደትም ለአንዱ ሲሰጥ ለሌላኛው “ከጁንታ ጋር ተባብረሃል“ በሚል ይከለከላል የምትለው ንግሥት “ትግራዋይ ነኝ ለሚል ሰው የሚታሰብ አይደለም። አዲስ መታወቂያ የሌለን ነዋሪዎችም እርዳታ ተከልክለናል። ምክንያቱን ስንጠይቅ ጁንታን ስትረዱ ነበር’ የሚል መልስ ነው የሚሰጡን” ብላለች።
የአላማጣ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ የማነ እንዳሚሉት የከተማዋ ሕዝብ ከ65,000 እስከ 73,000 ይገመታል። በአሁኑ ወቅት ግን ግማሽ የሚሆነው ተፈናቅሎ በማይጨው፣ መኾኒ እና ሌሎች አካባቢዎች ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ከንቲባ የሆኑት አቶ ኃይሉ አበራ በከተማው “በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር” የሚል አዲስ መታወቂያ እየተሰጠ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የማንነት ጉዳይ ገና ባልተወሰነበት እና በሕገ መንግስቱ መሠረት ይፈታል በተባለበት ሁኔታ ወቅት አዲሱን የአማራ ማንነት የሚገልጽ መታወቂያ መስጠት ሕገወጥ አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ ለከንቲባው አቅርበን ነበር።
“ቀድሞንም የታገልኩት እና እየጠየቅኩ ያለሁት ማንነቴን ለማስመለስ ነው። እኔ አማራ ነኝ ብያለሁ። ስለዚህ አሁን ያለው አስተዳደር ጊዜያዊ ቢሆንም የከተማው ነዋሪ በእጁ መያዝ ያለበት መታወቂያ ‘ሰሜን ወሎ ዞን የአላማጣ ከተማ አስተዳደር’ ሚል መሆን አለበት። ነገር ግን ይህ መታወቅያ አያስፈልገኝም የሚል ሰው አይገደድም” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
ትምህርት ቤቶች በአማርኛ እንዲያስተምሩ እየተደረገና ነባሮቹ የትግርኛ መጻሕፍቶች በአማርኛ እየተተኩ መሆናቸውን በማረጋገጥም “በአፍ መፍቻ ቋንቋው ስለተማረ ቅሬታ የሚያቀርብ ማግኘት አትችልም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ሲቀርብ ለነበረ ጥያቄ ነው መልስ እየሰጠን ያለነው” ብለዋል ከንቲባ ኃይሉ።
“ግዳጅ እና አስር”
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአላማጣ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዶ ነበር። እዚህም ላይ በግዳጅ እና በፍርሃት ሰልፉን የተቀላቀሉ ነዋሪዎች በሰልፉ እንደተሳተፉ እና አብዛኞቹ የሰልፉ ተሳታፊዎችም የከተማዋ ነዋሪዎች አይደሉም የሚሉ አሉ።
“ነዋሪውን በግድ ነው እንዲወጣ ያደረጉት። በሰልፉ ያልተሳተፉ ‘ጁንታ ነህ’ እያሉ ከባድ የገንዘብ ቅጣት ጥለውበታል። ነገር ግን አብዛኛው ሰው ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሰበ ነው። ከቆቦ፣ ከዋጃ፣ ከወርቅዬ፣ ከጎቢዬ እስከ ወልድያ በመኪና ጭነው ባስመጧቸው ሰዎች ሰልፉን ትልቅ ለማስመሰል ሞክረዋል” ይላል ስሙ መግለጽ ያልፈለገ ነዋሪ።
ንግሥትም በተመሳሳይ “ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ያልተገኘን ሰው ‘ጁንታ ነው፤ ጀርባው ሊጠና ይገባል’ ሲባል ጊዜ ፍርሃት ያደረባቸው ነዋሪዎች ወደ ሰልፉ በመሄድ ተሳትፈዋል። ፈርተው ሰልፉን ከተቀላቀሉት ነዋሪዎች መካከልም አንዳንዶቹን ‘ፀጉር ለወጥ’ በሚል ታስረዋል” ስትል ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግራለች።
ከንቲባ ኃይሌ አበራ ግን “ይህ ከእውነት የራቀ ነው። ማንም ነዋሪ በግዳጅ ሰልፍ እንዲወጣ አልተደረገም። ለድጋፍ ሰልፉ ከተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ተጭኖ የመጣም ሕዝብ የለም። ይህ እንዳይባልም ቀድመን በማሰብ በሰልፉ ዕለት ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ መንገዶችን ሁሉ ዝግ አድርገናል” በማለት ይቃወማሉ።
አላማጣ ከተማ ጦርነቱ እስከጀመረበት ድረስ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስር ትተዳደር የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ የከተማዋ ነዋሪ ትግራዋይ ማንነት እንዳላቸው የቀድሞው ከንቲባ አቶ የማነ ይናገራሉ።
የወቅቱ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ግን “እስከ 95 በመቶ የሚደርሰው የከተማዋ ነዋሪ በማንነቱ አማራ በመሆኑ ለጥያቄዎቹ መልስ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ቆይቷል። ስለዚህ አንድም ነዋሪ አማራ እንዲሆን አላስገደድንም” ብለዋል።
አክለውም “በዚህች ከተማ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ዛሬም በነፃነት እየኖሩ ነው። ነገር ግን በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ማንኛውም ሰው በሕግ ተጠያቂ ይሆናል። የፖለቲካ እስረኛ የሚባል የለንም። ከ2,200 በላይ የነሱ ሰዎች [የትግራይ] ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ከታሰሩ በኋላ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር እነሱም ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ ጠይቀው ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል” ሲሉም አክለዋል ከንቲባ ኃይሉ።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ የገለጹልን ያነጋገርናቸው ሰዎች ከእስር ለመፈታት “ትንሽ ከሚባለው 1,000 ብር እስከ 32,000 ብር” እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ክፍያው የሚከፈለው ለታጣቂዎች እና ለባለስልጣናት እንጂ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዳልሆነም ገልጸዋል።
ክሱን ያስተባበሉ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው “የሰዓት እላፊን ሕግ ጥሰው የተገኙና ቀላል ወንጀሎች የፈጸሙ ግለሰቦች በማኅበራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው ይቀጣሉ። ነገር ግን በማንነታቸው እና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለዚህ የተጋለጡ አሉ የሚለው ፍፁም ሐሰት ነው” ብለዋል።