የሩበን አሞሪም ማንቸስተር ዩናይትድ አንፊልድ ላይ ያሳየው "ተጋድሎ"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ወደ አንፊልድ አቅንቶ ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል ጋር ያደረገው ጨዋታ 2 አቻ ተጠናቋል።
በአዲሱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የሚመራው ዩናይትድ ከሰሞኑ ደካማ አቋሙ በተቃራኒ መንፈሰ ጠንካራ ሆኖ ተስተውሏል ይላል የቢቢሲ ስፖርት ፀሐፊው ፊል ማክነልቲ።
ዩናይትድ የእሑድ ምሽቱን ጨዋታ ቢሸነፍ ከአውሮፓውያኑ1979 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በመሸነፍ የራሱን ታሪክ ያበላሸ ነበር።
አንፊልድ ላይ በነበረው ጨዋታ ዩናይትድ በ52ኛው ደቂቃ በተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ጎል ጨዋታውን መምራት ይዞ ነበር።
ከሰባት ደቂቃ በኋላ ሊቨርፑል በኮዲ ጋክፖ አማካይነት አቻ ሲሆን ሞሐመድ ሳላህ ከ20 ደቂቃዎች በኋላ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል ሊቨርፑልን መሪ የሚያደርግ ጎል አስቆጥሯል።
ሞ ሳላህ በ175 ጎሎች የፕሪሚዬር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ ላይ ከፈረንሳዊው የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች ቲየሪ ሄንሪ እኩል ተቀምጧል።
ምንም እንኳ ዩናይትድ በጨዋታው እየተመሩ ቢሆንም አማድ ዲያሎ ባስቆጠራት ጎል አቻ በመሆን ከአንፊልድ ከባድ የሚባል አንድ ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል።
የዩናይትዱ ተከላካይ ሃሪ ማጓየር በጨዋታው መገባደጃ ቡድኑ አሸናፊ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢያገኝም አልተጠቀመበትም።
ብዙዎች ዩናይትድ በሊቨርፑል በሰፊ የጎል ልዩነት ይሸነፋል የሚል ግምት ነበራቸው። ይህ ግን አልሆነም ይላል ፊል። አንፊልድ ላይ ከፍተኛ ተጋድሎ ማሳየታቸውን ይናገራል።
በርካቶች ዩናይትድ በአዲሱ አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም ስር እንዲህ ያለ ተጋድሎ አሳይቶ አያውቅም ሲሉ የቡድኑን ጥንካሬ ሲያደንቁ ተስተውለዋል።
ሞ ሳላህ ሊቨርፑልን ቀዳሚ ሲያደርግ ሽንፈት የማይቀር ቢመስልም ዩናይትድ ግን አቻ ከማድረግ አልፎ ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ሙከራ ሲያደርጉ ነበር፥
ማንቸስተር ዩናይትድ ከሰሞኑ ባሳየው አቋም ምክንያት ከፍተኛ ትችት ሲያስተናግድ ቆይቷል።
በዩናይትድ በኩል ማኑኤል ኡጋርቴ፣ ብሩኖ ፈርናንዴዝ እና ኮቢ ሜይኑ አንፊልድ ላይ ባሳዩት ብቃት አድናቆት የተቸራቸው ተጫዋቾች ናቸው።
በተቃራኒው ወደ ስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ይሄዳል የሚል ወሬ የተናፈሰበት የሊቨርፑሉ ተከላካይ ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ ትችት ደርሶበታል።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሊቨርፑል አሁንም የሊጉን ሰንጠረዥ እየመራ ሲሆን በከአርሰናል በ6 ነጥብ ከፍ ብሎ ይገኛል።
አርሰናል በ40 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሰኞ ምሽት የሚጫወተው ኖቲንግሀም በ37 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ነው።












