እነማን የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርን ከፍተኛ የሥልጣን ቦታን ሊያገኙ ይችላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸውን የሚቀላቀሉ ሹመኞችን እያስታወቁ ነው። የጽሕህት ቤት ኃላፊ፣ የድንበር ኃላፊ፣ የተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደርን እና የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ኃላፊ ሚሆኑት ግለሰቦችን ይፋ አድርገዋል።
የተመራጩ ፕሬዝዳንት ጥር 20 በድጋሚ ወደ ዋይት ሐውስ ይመለሳሉ። ቀደም ብለው ግን የተለያዩ ዕጩዎችን እያነሱ እየጣሉ ነው።
የምርጫ ቅስቀሳቸውን የመሩት ሱዚ ዊልስ የመጀመሪያዋ ሴት የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። የመጀመሪያው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን ከጎናቸው ነበሩት ቶም ሆማን ደግሞ ከድንበር እና ከስደት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።
ፕሬዝዳንቱ አራት ሺህ የሚጠጉ ፖለቲካዊ ሹመቶችን የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ሂደት ብቻ ወራትን ሊወስድ ይችላል። ሹመት የተሰጣቸውን እና ከዚህ በኋላ ለከፍተኛ ኃፊነት የሚጠበቁ ሰዎችን አንድ በአንድ እንመለከታለን።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ - ማይክ ዋልትስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፍሎሪዳው የኮንግረስ አባል ማይክል ዋልትስ ቀጣዩ የትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ተደርገው እንደሚመርጡ ይጠበቃል ሲሉ ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው አሜሪካ ላይ ሊፈጠሩ በሚችሉ የተለያዩ ስጋቶች ዙሪያ ፕሬዝዳንቱን ያማክራሉ። ዋልትስ በእስራኤል፣ በዩክሬን እና በሩሲያ ጦርነቶች ላይ የአሜሪካን አቋም የሚዘውሩ ይሆናል።
ይህ ሥልጣን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሹመት ተደርጎ ከመወሰዱም በላይ ለሹመቱ የሴኔቱን ይሁንታ አይፈልግም።
የድንበሩ ቄሳር - ቶም ሆማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህ ወሳኝ ሥራ ነው። ምክንያት ከተባለ ደግሞ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕገ ስደተኞችን ለማባረር የገቡትን ቃል ለመጠበቅ የሚረዳቸው ሹመት ነው።
ሆማን በድንበር ቁጥጥር ላይ “ቁርጠኛ” ናቸው ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው የራሳቸው በሆነው የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ አስታውቀዋል።
የቀድሞው የፖሊስ መኮንን በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ የበላይ ቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት (አይሲኢ) ውስጥ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። ስድትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ትዕግስት እንዳይኖር ሲወተውቱ ይደመጣሉ።
“ትራምፕ በጥር ወር ተመልሶ ፕሬዝዳንት ይሆናል፤ እኔም እመለሳለሁ” ሲሉ ባለፈው ሐምሌ ተናግረዋል። “ይህች አገር አይታ የማያውቅ ትልቁን የማባረር ሥራ እሠራለሁ” ሲሉም ዝተው ነበር።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር - ኤልሲ ስቲፋኒክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ቢቢሲ አጋር ሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ የኒውዮርክ ኮንግረስ አባሏ በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደርነትን ቦታ አግኝተዋል።
በትራምፕ የ2019 የክስ ችሎት እና ዘንድሮ ደግሞ የኮሌጅ መሪዎችን በተቋሞቻቸው ውስጥ ባለው ፀረ ሴማዊነት ዙሪያ ጠንካራ ጥያቄዎችን በማቅረብ ስቴፋኒክ የመገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል።
ትራምፕ ለኒውዮርክ ፖስት በሰጡት መግለጫ “ኤልሲ በሚያስገርም ሁኔታ ጠንካራ፣ ኃይለኛ እና ብልህ አሜሪካዊ ነች” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት አምባሳደርነት ሥራን ጨምሮ አንዳንድ አሜሪካ የፖለቲካ ሹመቶች የአገሪቱን ሴኔት ይሁንታን ይፈልጋሉ። ቀጣዩ የሴኔት መሪ ከተለመደው የይሁንታ ሂደት ውጪ ሹመት እንዲፈቅድ ትራምፕ ጠይቀዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ኃላፊ - ሊ ዜልዲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊ ዜልዲን የቀድሞ የኒውዮርክ ኮንግረስ አባል ነበሩ። የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲን ለመምራት መስማማታቸው እሳቸውም ሆኑ ትራምፕ አረጋግጠዋል። ለዚህ ሹመትም የሴኔቱ ይሁንታ ይጠበቃል።
ሹመቱ የአሜሪካ የአየር ንብረት ፖሊሲን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል።
“የአሜሪካንን የኃይል የበላይነት እናስመልሳለን፤ የአሜሪካዊያንን ሥራ ለመመለስ የመኪና ኢንዱስትሪያችንን እናነቃቃለን፣ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሪ እናደርጋታለን" ሲሉ ዜልዲን በኤክስ ላይ አስፍረዋል። “እግረ መንገዳችንንም የንጹህ አየር እና ውሃ ተደራሽነትን እናሰፋለን” ሲሉ አክለዋል።
ዜልዲን ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የትራምፕ ደጋፊ ናቸው። የ2020ውን የምርጫ ውጤት በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ደብዳቤ ከጻፉ 126 የሪፐብሊካን ኮንግረስ አባላት አንዱ ናቸው።
ከ2015 እስከ 2023 የኮንግሬስ አባል ሆነው አገልግለዋል። ዜልዲን የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲዎችን እንዳይስፋፉ ድምጽ ሰጥተዋል። ኃፊነታቸውን ከሚረከቡበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ “ደንቦችን ወደ ኋላ ለመመለስ” ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ከሰጡት ድምጽ በመነሳት ከአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ከፍተኛ ውጤት አላገኙም።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ - ሱዚ ዊልስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ የምርጫ ዘመቻው ተባባሪ ሊቀመንበር የሆኑት ሱዚ ዊልስ እና ክሪስ ላሲቪታ ተመራጩ ፕሬዝዳንት በካማላ ሃሪስ ላይ ለተቀዳጁት ድል የጀርባ አጥንት ነበሩ።
ከድላቸው በኋላ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር “የበረዶዋ እመቤት” በማለት ያላቸውን የመረጋጋት ባህሪ ገልጸዋል። ከጀርባ ሆነው መሥራት እንደሚወዱም ተናግረዋል። ዊልስ በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የመጀመሪያዋ ተሿሚ ሆነዋል።
የጽህፈት ቤት ኃላፊነት ሥራ የፕሬዝዳንቱ ከፍተኛ ረዳት መሆን ነው። በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የሚደረጉ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን መቆጣጠር እና የፕሬዝዳንቱን ሠራተኞችንም ማስተዳደርን ያካትታል።
የ67 ዓመቷ ዊልስ ለአስር ዓመታት በሪፐብሊካን ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈዋል። ከሮናልድ ሬጋን የተሳካ የ1980 ፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ዘመቻ እስከ ሪክ ስኮት እና ሮን ዴሳንቲስን የፍሎሪዳ ገዢነት ምርጫም ሚና ነበራቸው።
ሪፐብሊካኖች ተሰሚነት እንዳላቸው እና በትራምፕ ዙሪያ ያሉትን ትልልቅ ፖለቲከኞች የመምራት ችሎታ እንዳላቸው ተናግረዋል። ይህም የቀደሙት አራት የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ያልቻሉትን አመራርነት እንዲከውኑ ይረዳቸዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፍትህ መሥሪያ ቤት ኃላፊን ለመሾም የሚደረገውን ፈተና ያህል ለትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ወሳኝ የሚሆን ሹመት ሊኖር አይችልም።
ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር እና ጄፍ ሴሽንስ ጥሩ ግንኙነት አልነበራቸውም። ትራምፕ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሹመቱን እንደ “ተናካሽ ውሻ” የሚጠቀም ታማኝ ሰው እንዲመርጡ ሊገደዱ ይችላሉ የሚል ሰፊ ግምት አለ።
ለካቢኔ ሹመት ሊታጩ ይችላሉ ከተባሉ ስሞች መካከል አይሊን ካነን ይገኙበታል። ግለሰቡ ምሥጢራዊ ሰነዶችን በተመለከተ የቀረበባቸውን ክስ ውድቅ ያደረጉ የፌዴራል ዳኛ ናቸው።
ትራምፕ የ2020 ምርጫ ውጤትን ለመቀልበስ አድርገዋል የተባሉት ጄፍሪ ክላርክ፤ እንደ ትራምፕ የተከሰሱ እና ከኃላፊነት የተነሱት የቴክሳሱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኬን ፓክስተን፤ በትራምፕ ጥያቄ ሴሽንስ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ለሦስት ወራት ተጠባባቂ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ያገለገሉት ማቲው ዊትከር ይጠቀሳሉ።
በአንድ ወቅት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ኒል ጎርሱች ፀሐፊ ሆነው ያገለገሉት እና በትራምፕ ተቺዎች እና ጋዜጠኞች ላይ ማስፈራሪያ የሰነዘሩት የቀኝ ክንፍ አቀንቃኙ ማይክ ዴቪስ እና በትራምፕ የበጀት ቢሮ ውስጥ ያገለገሉት እና ፕሬዝዳንቱ ከፍትህ ቢሮ ውሳኔዎች የሚርቁበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መስፈርት እንደሌለ የተከራከሩት ማርክ ፓኦሌታ ይገኙበታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የፕሬዝዳንቱ የውጭ ጉዳይ ዋና አማካሪ ይሆናል። ወደ ባሕር ማዶ ሲጓዝ አገሪቱን የወከለው የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሆኖም ያገለግላል።
እስከ ቅርብ ጊዜ የትራምፕ ምክትል ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ የታሰቡት የፍሎሪዳው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ቁልፍ ለሚባለው የካቢኔ ሹመት ስማቸው በቀዳሚነት ይነሳል።
የ53 ዓመቱ ሩቢዮ ከቻይና ጋር በተያያዘ ጠንከር ያለ አመለካከከት አላቸው። እአአ በ2016 ትራምፕ የሪፐብሊካን ተወካይ እንዳይሆኑ ጠይቀዋል። ከዚያ በኋላ ግን አቋማቸውን አስተካክለዋል። የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ከፍተኛ አባል እና የንግድ ምክር ቤቱ የስለላ ቡድን ምክትል ሊቀመንበር ናቸው።
ለሥራው ዕጩ ከሆኑ ተፎካካሪዎች መካከል የባዮቴክ ሥራ ፈጣሪ እና የ2024 የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ቪቪክ ራማስዋሚ፤ የትራምፕ የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሮበርት ኦብራይን፤ በትራምፕ አስተዳደር ዘመን የጃፓን አምባሳደር የነበሩት የቴኒሲው ሴናተር ቢል ሃገርቲ እና በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን የኢራን ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ብራያን ሁክ ይገኙባቸዋል።
ባልተጠበቀ መልኩ ግምት ያገኙት በጀርመን አምባሳደር፣ የባልካን ልዩ መልዕክተኛ እና የብሔራዊ መረጃ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ሪቻርድ ግሬኔል ናቸው።
ትራምፕ በ2020ው ምርጫ የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመቀልበስ ባደረጉት ጥረት ላይ የ58 ዓመቱ ግሬኔል ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው። ትራምፕ ባለፈው ጥር ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጋር ባደረጉት የግል ስብሰባ ላይም ተሳትፈዋል።
የስለላ/የብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊነቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የግሬኔል የተዋጊነት ባህሪ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ይልቅ ለብሔራዊ ደኅንነት አማካሪነት የበለጠ ተስማሚ ያደርጋቸዋል። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በተለየም ቦታው የሴኔት ይሁንታ አያስፈልገውም።
በሁለተኛው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን ለቦታው በቀዳሚነት ከታጩት መካከል የቀድሞ የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ፤ የትራምፕ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ኪት ኬሎግ፤ የቀድሞው የመከላከያ ቢሮ ኃላፊ ኤልድሪጅ ኮልቢ እና በትራምፕ የመጨረሻዎቹ የሥልጣን ወራት በብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ያገለገሉት ካሽ ፓቴል ይገኙበታል።
ለጆ ባይደን አስተዳደር የሚደረገውን የሥልጣን ሽግግር ለማገድ ድጋፍ ያደረጉት የ44 ዓመቱ ፓቴል የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ኃላፊ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
እአአ በ2017 ዕጩ ያደረጓቸው እና ኋላ ላይ ከእሳቸው በተቃራኒ የቆሙትን የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዳይሬክተሩ ክሪስ ሬይን እንደሚያባርሩ ትራምፕ ተናግረዋል። ቀደም ሲል በትራምፕ የአሜሪካ ጠበቃ ሆነው የተሾሙት ጄፍሪ የንሰን ይተኳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የመከላከያ ሚንስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ በመጨረሻ የሥስልጣን ወራቶቻቸው ተጠባባቂ የመከላከያ ኃላፊ አድርገው ሾሟቸውን ክርስቶፈር ሚለር ወታደራዊ ኃይሉን እንዲመሩ ዕጩ ተደርገዋል።
ጡረተኛው ወታደር የብሔራዊ የፀረ-ሽብርተኝነት ማዕከልን ይመራሉ። በቅርቡም በሁለተኛው ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ይተገበራል ያሉትን አወዛጋቢውን የፕሮጀክት 2025 የመከላከያ ምዕራፍ ቢጽፉም ትራምፕ ግን ራሳቸውን ከሰነዱ አግልለዋል።
በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የጦሩ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆኑት የፍሎሪዳው የሕግ አውጪ ማይክል ዋልትዝ እና ሮበርት ኦብራይንም ከኃላፊነቱ ጋር ስማቸው ተያይዟል።
የግምጃ ቤት ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትራምፕ ከቻይና ጋር ተፈጠረውን የታሪፍ ግብግብ በመምራት እና በነጻ ንግድ ዙሪያ ጥያቄ የሚያነሱትን ሮበርት ላይትሂዘርን የአሜሪካ የንግድ ተወካይ እና ዋና የፋይናንስ ኃላፊ አድርገው እንደሚቆጥት ተዘግቧል።
ሌሎች አራት ግለሰቦችም ለቦታው ሊሾሙ እንደሚችሉ ተገምቷል። ቢሊየነሩ የሄጅ ፈንድ ሥራ አስኪያጅ፣ ምርጫ ዋና የገንዘብ አሰባሳቢ እና የተመራጩ ፕሬዝዳንት የኢኮኖሚ አማካሪ ስኮት ቤሴንት ይጠቀሳሉ።
ሌላኛው የሄጅ ፈንድ ከፍተኛ የገንዘብ ለጋሽ ጆን ፖልሰን፤ የቀድሞው የሴኪውሪቲስ እና ኤክስቼንጅ ኮሚሽን (ኤስኢሲ) ሊቀመንበር ጄይ ክላይተን እና የፎክስ ቢዝነስ ኔትዎርክ የፋይናንሺያል ተንታኝ ላሪ ኩድሎ ተጠቃሾች ናቸው።
የንግድ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ የሽግግር አስተዳደር ሊቀ መንበር የሆኑት ሊንዳ ማክማሆን በካቢኔው ውስጥ የአሜሪካን የንግድ ተቋማትን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለመምራት ቁልፍ ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል። በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን የአነስተኛ የንግድ ሥራ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
ይህንን ኃላፊነት ቦታ ሊረከቡ ይችላሉ የተባሉት ሌሎች ግለሰቦች ደግሞ ብሩክ ሮሊንስ፣ ሮበርት ላይትሄዘር፣ እና ለአጭር ጊዜ በአሜሪካ ሴኔት ያገለገሉት ሐብታሟ የንግድ ሰው ኬሊ ሎፍለር ናቸው።
የአገር ውስጥ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ ዳኮታ ገዥ ሆኑት ክሪስቲ ኖኤም የቤት ውሻቸውን መግደላቸውን በማመናቸው ምክንያት የትራምፕ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዳይወዳደሩ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
ለፕሬዝዳንቱ ያላቸው ታማኝነት የሕዝብ መሬትን እና የተፈጥሮን ሃብትን በሚያስተዳድረው የአገር ውስጥ ሚኒስትርን እንዲመሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ለኃፊነቱ ከሰሜን ዳኮታ ገዥ ደግ በርጉም ጋር ሊፎካከሩ ይችላሉ።
የኢነርጂ ሚንስትር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳግ በርጉም የኢነርጂ ኃላፊ ለመሆንም ተፎካካሪ ናቸው። ትረምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ነዳጅ ቆፍረው ለማውጣት የገቡትን ቃል በማስፈጸም የአሜሪካን ኢነርጂ ፖሊሲ ለማሻሻል ይሠራሉ።
እአአ በ2001 አነስተኛ ኩባንያቸውን ለማይክሮሶፍት የሸጡት የሶፍትዌር ሥራ ፈጣሪው በርጉም፤ በ2024 ሪፐብሊካን ለመወከል መወዳደር ቢጀመሩም በጊዜ አቋርጠው ትራምፕን ደግፈዋል። ባላቸው ስብዕና እና ባፈሩት ሐብትም ትራምፕ ዓይን ውስጥ ገብተዋል።
የቀድሞው የኢነርጂ ሚኒስትር ዳን ብሮውይልም ከዕጩዎቹ መካከል አንደሆኑ ተነግሯል።
የፕሬስ ክፍል ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የ27 ዓመቷ ካሮሊን ሌቪት ትራምፕን በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ብሔራዊ የፕሬስ ሴክሬታሪ በመሆን አስደምማቸዋል። ካሮሊን የዋይት ሐውስ ረዳት ፕሬስ ሴክሬተሪ ሆና ያገለገለች ሲሆን፣ የአዲሱ አስተዳደር ቃል አቀባይ ልትሆን ትችላለች።
ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁኒየር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አር.ኤፍ.ኬ ጁኒየር የአካባቢ ጥበቃ ጠበቃ ናቸው። ክትባት ላይ ባላቸው ጥርጣሬ ደግሞ ዝና አትርፈዋል። የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የወንድም ልጅ ናቸው።
የጤና እና የሰብአዊ አገልግሎት ቢሮን ለመምራት ከታጩት መካከል ናቸው። ይህንንም ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ቅርብ የሆኑ ብዙ ሰዎች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።
የ70 ዓመቱ ኬኔዲ ከሕክምና ጋር በተያያዘ ሥልጠና ባይኖራቸውም በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ “የሕዝብ ጤና ኃላፊ” ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሹመቱ በጤና እና ሰብአዊ አገልግሎት ክፍል ውስጥ ከሚያስገኝላቸው ኃላፊነት በተጨማሪ ኬኔዲ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ፣ በበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) እና በምግብ እና መድኃኒት ደኅንነት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) ፖሊሲ ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ።
ኢላን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዓለማችን ቁጥር አንድ ከበርቴ የሆነው ኢላን መስክ ትራምፕ እንዲመረጡ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር አፍስሷል። ኩባንያዎቹ ቴስላ፣ ስፔስኤክስ እና ኤክስ የሚመለከቱት ደንቦችን የመቅረጽ ሥልጣን ይኖረዋል በሚል ተቺዎቹ ተግረዋል።
እሱ እና ትራምፕ አዲሱን “ዲፓርትመንት ኦፍ ኤፊሸንሲን” ይመራዋል የሚል ሃሳብ አላቸው። በዚህም ወጪን በመቀነስ “ግዙፍ እና በፌደራል ደረጃ ያለውን ቢሮክራሲ” ያስተካክላል ተብሏል።
የኤጀንሲው ምህፃረ ቃል የሆነው ዶጅ (DOGE) ቀደም ሲል መስክ ካስተዋወቀው ክሪፕቶከረንሲ ጋር ይመሳሰላል።
የ53 ዓመቱ መስክ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ላይም ሚና መጫወት ይችላል። ረቡዕ ዕለት ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ የስልክ ውይይት ወቅት ተሳትፊ ነበር።
በአዲሱ አስተዳደር ውስጥ ሹመት የማያገኙ አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ “የቀድሞዋን በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊን እና የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮን” በድጋሚ ወደ አስተዳደራቸው እንደማይጋብዙ ትሩዝ ላይ ጽፈዋል።
የረዥም ጊዜ አጋራቸው የሆነው ሮጀር ስቶን ሁለቱንም ከትራምፕ አጀንዳ ጋር የሚቃረኑ “አስከፊ አምስተኛ አምድ” ሊፈጥሩ የሚችሉ መሆናቸውን ከገለጹ ከአንድ ቀን በኋላ ነው ትራምፕ ሃሳባቸውን የገለጹት።
ሄሊ በ2024 የሪፐብሊካን ምርጫ ወቅት ትራምፕን ከመፎካከር ባለፈ አጥብቀው ተችተዋል። ፖምፒዮ ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ከፍተኛ ግምት ነበር።
የአርካንሳስ ሴናተር ቶም ኮተን በበኩላቸው በአዲሱ ሴኔት ውስጥ ሦስተኛውን ከፍተኛ ሥልጣን እንደሚይዙ በመገመቱ ራሳቸውን ከትራምፕ ሹመት አርቀዋል።
የዩታ ግዛት ሴናተር የሆኑት ማይክ ሊ “የምፈልገው ሥራ አለኝ” ሲሉ ለዴዘርት ኒውስ የተናገሩ ሲሆን፣ ሪፐብሊካኖች ወደ ዋሽንግተን የተመለሱበትን ሙሉ ሥልጣን መጠቀም አለባቸው ብለዋል።















