የአውስትራሊያ ፖሊስ ከባሕር ላይ የታደጋቸው በዕጽ ዝውውር ተጠርጣሪ ሆነው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, AUSTRALIAN MARITIME SAFETY AUTHORITY
ከቀናት በፊት የአውስትራሊያ ፖሊስ ከባሕር ላይ የታደጋቸው ሦስት ሰዎች የአደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪ ተጠርጣሪዎች ሆነው ተገኙ።
እነዚህ ሦስት ሰዎች ከሁለት ሳምንታት በፊት በምዕራብ አውስትራሊያ ባሕር ውስጥ በረዶ መያዣ ሳጥን ላይ ተንጠላጥለው ነበር ፖሊስ ያገኛቸው።
ፖሊስ ሦስቱን ግለሰቦች ሕይወታቸውን ከታደጋቸው በኋላ አሳ ለማጥመድ ከወጡ በኋላ ጀልባቸው መስጠሟን እንደነገሩት በወቅቱ ይፋ አድርጎ ነበር።
ፖሊስ ግለሰቦቹ በሕይወት ሊገኙ የቻሉት የአደጋ ጊዜ መንሳፈፊያ በማጥለቃቸው እንዲሁም በአደጋ ግዜ መገኛ የሚጠቁም መሳሪያ በመያዛቸው ነው በማለት ለሌሎች ትምህርት ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ አወድሷቸው ጨምር ነበር።
ይሁን እንጂ ፖሊስ ሦስቱን ግለሰቦች ከባሕር ታድጎ ካሰናበታቸው በኋላ ባሕር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ኮኬይን መገኘቱን ተከትሎ የእስር ትዕዛዝ አውጥቶባቸዋል።
የአገሪቱ ፖሊስ ሦስቱ ሰዎች በዓለም አቀፍ የዕጽ ዝውውር ወንጀል እየፈለጋቸው መሆኑን እና እጃቸውን ለፖሊስ እንዲሰጡ ጠይቋል።
የአውስራሊያ ፌደራል ፖሊስ ሰዎቹ ባሕር ላይ ከተገኙ ከስድስት ቀናት በኋላ ኮኬይን የያዙ በጥቁር ላስቲክ የተለበጡ ጥቅሎች ባሕር ላይ መገኘታቸውን አስታውቋል።
በቀጣይ ቀን ደግሞ እያንዳንዳቸው 40 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 8 የኮኬይን ጥቅሎችን የሰመጠ ጀልባ ውስጥ ማግኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ሦስቱ ግለሰቦች ከባሕር ላይ አደገኛውን ዕጽ በጀልባ ጭነው ወደ ባሕር ዳርቻ ሲመጡ አደጋ እንዳጋጠማቸው ያምናል። ይሁን እንጂ አደገኛ ዕጹ በቅድሚያ እንዴት ባሕር ላይ ሊደርስ እንደቻለ ግልጽ አይደለም።
ምርማሪ ፖሊስ ሜት ስቲፒኖቪች፣ ካርል ዊትበርን እና አሪስቲደስ አቭሎንቲስ የተባሉ ከ36 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ሕዝቡ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቋል።
የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ግራሚ ማርሻል የኮኬይኑ መያዝ ለዕጽ አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ኪሳራ ነው ብለዋል።
ፖሊስ ዕጹ ባይያዝ ኖሮ ከወንጀል፣ ከጤና መቃወስ እና በምርታማነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት 235 ሚሊዮን ዶላር ይገመታል ብሏል።












