ተራራ ሲወጣ ከ600 ሜትር ከፍታ የወደቀው ግለሰብ በሕይወት ተረፈ

ታራናኪ ተራራ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

ታትሟል

በኒው ዚላንድ ተራራ እየወጣ የነበረ ግልሰብ ከ600 ሜትር ከፍታ ወድቆ በሕይወት ተረፈ።

ከተራራው ሲወድቅ የገጠመው መጠነኛ ጉዳት ብቻ ነበር።

ታራናኪ ከተባለ ተራራ ላይ የወደቀው ግለሰቡ ለስላሳ የበረዶ ክምር ላይ መውደቁ ነፍሱን እንዳዳነው ፖሊስ ገልጿል።

የግለሰቡ በሕወት መትረፍ “ተዓምራዊ” ነው ተብሏል።

ፖሊስ እንዳለው “በሕይወት በመትረፉ ዕድለኛ ነው”።

የወደቀበት ርቀት ከዓለም ትልቅ ሕንጻዎች አንዱ ከሆነው የሳዑዲ አረቢያው፣ መካ ክሎክ ሮያል ታወር ርዝመት ጋር ይስተካከላል።

በቡድን ተራራ እየወጡ ሳለ ነበር ግለሰቡ እኩል ቀን ገደማ የወደቀው።

“ጓደኛቸው ሲወድቅ ካዩ በኋላ ተራራ እየወጡ ከነበሩት አንዱ ወደታች ወርዶ ጓደኛውን ፈልጓል” ሲል ፖሊስ ገልጿል።

በተራራው ላይ የሚገኙ ነፍስ አድን ሠራተኞች የወደቀበት ቦታ አግኝተውታል።

በኒው ዚላንድ አደገኛ ከሚባሉት ተራሮች አንዱ ይኸው ታራናኪ ተራራ ነው።

እአአ በ2021 ሁለት ሰዎች ተራራውን ሲወጡ ወድቀው ሞተዋል። ተጓዞቹ የወደቁት ግለሰቡ የወደቀበት ቦታ ነው።

በኒው ዚላንድ ሰሜናዊ ደሴት የሚገኘው ተራራው ታቹ እሳተ ገሞራ ነው።

የተራራው የደኅንነት ካውንስ እንዳለው፣ ተራራው ከሌሎች ተራሮች ያለው ርቀት፣ ለባሕር ዳርቻ ቅርብ መሆኑ፣ እና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ የተለየ መሆኑ በቦታው የተለያየ የአየር ሁኔታ እንዲፈጠር አስችሏል።

የአካባቢው የአየር ሁኔታ አካባቢውን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ተራራውን የሚወጣ ሰው አንዳችም ስህተት ቢሠራ የሚጠብቀው አደጋ የከፋ ነው።

ከዚህ ቀም ተራራ ሲወጡ ከከፍታ ወድቀው ከተረፉ አንዱ የስኮትላንዱ ስገር ቾይኒች ሞር ሲሆን፣ 300 ሜትር ቁልቁል ነበር የወደቀው።

ካናዳ ውስጥ ሎፍሪ የተባለ 3,423 ሜትር የሚረዝም ተራራ ሲወጣ ከ400 ሜትር ከፍታ ወድቆ የተረፈው ግለሰብም ይጠቀሳል።