በትግራይ የጸጥታ ኃይሎች አንድን ወጣት በዱላ ደብድበው መግደላቸው ተነገረ

የሃይለ አያልነህ አስከሬን ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ ቤተሰብ ሲላክ
የምስሉ መግለጫ, የሟች ቤተሰቦች ለአያልነህ ሞት ምክንያት ይፋዊ ሪፖርት ባያገኙም አስከሬኑን ከአይደር ሆስፒታል ተቀብለው ወደ ትውልድ ቦታው ወስደዋል።
ታትሟል

በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን ፅምብላ ወረዳ አንድ የ35 ዓመት አርሶ አደር በጸጥታ ኃይሎች ተደብድቦ ሕይወቱ ማለፉን የሟች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናገሩ።

የፅምብላ ወረዳ ዘናቁሌ ቀበሌ ነዋሪ የነበረው ሃይለ አያልነህ በድብደባ ሕይወቱ ያለፈው በጦር መሳሪያ ንግድ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር ከዋላ በኋላ ነው።

የወረዳው የጸጥታ ኃይሎች በግብርና ስራ ተሰማርቶ የነበረን ወጣት በጦር መሳሪያ ንግድ ጠርጥረው በቁጥጥር ስር ያውሉት እንጂ በጦር መሳሪያ ንግድ ላይ ተሰማርቶ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ እንዳልተገኘ የቤተሰብ አባላት ተናግረዋል።

የሟች ሃይለ አያልነህ ወንድም የሆነው በሪሁ አያልነህ ወንድሙ በቁጥጥር ሥር የዋለው በድብዳበ ቃሉን በሰጠው ሰው ጥቆማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በፅምብላ ወረዳ ታጣቂዎች ሽጉጥ በመሸጥ የጠረጠሩትን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውለው በኃይል ከገረፉት በኋላ ሃይለ አያልነህን ጠቆመ። ከዚያ በኋላ የጸጥታ ኃይሎች ሃይለ ሽጉጥ ይሸጥ እንደነበረ እንዲያምን ከልክ በላይ በመደብደባቸው ልጁ ሕይወቱ አልፏል” ብሏል።

ሃይለ በጸጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ድብደባ ከደረሰበት በኋላ ሕይወቱ ወዲያውኑ ባለማለፉ ቤተሰቦቹ ወደ ሕክምና እየወሰዱት ነበር። ነገር ግን የደረሰበት ድብደባ ከፍተኛ በመሆኑ የሕክምና ቦታ ሳይደርስ መንገድ ላይ ሕይወቱ አልፏል።

የሟች ቤተሰቦች ሁኔታውን ለወረዳው ኃላፊዎች ያሳወቁ ሲሆን፣ የወረዳው ፖሊስ አስከሬኑን ለምርመራ ወደ መቀሌ አይደር ሆስፒታል ከላከ በኋላ ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ የፅምብላ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤትን ለመጠየቅ ያደረግው ጥረት አልተሳካም።

የሟች ወንድም እንደሚሉት አያልነህ በቁጥጥር ሥር የዋለውን በሥራ ቦታው የአረም ስራ ሳለ መሆኑን ይገልጻል።

"አረም ላይ እያለ ነው የወሰዱት። . . . እሱን ለማስፈታትም 50,000 ብር እንድንከፍል ተጠይቀን ነበር” ብሏል።

"ወንድማችን ተገድሏል፤ አሟሟቱም በጣም ያሳዝናል። በዚህም ምክንያት ሂደቱ መመርመር አለበት" ብለዋል ሌላኛው የሟች ቤተሰብ ዳኛው ተስፋይ።

የሟች ቤተሰቦች
የምስሉ መግለጫ, ዳኛው ተስፋይ (ግራ) እና የሟች ወንድም በሪሁ አያለነህ (ቀኝ)

የሟች ቤተሰቦች ለአያልነህ ሞት ምክንያት ከሐኪም ይፋዊ ሪፖርት ባያገኙም አስከሬኑን ከአይደር ሆስፒታል ተቀብለው ትናንት ወደ ትውልድ ቦታው ወስደዋል።

ለሁለት ዓመታት ከዘለቀው ከርስ በበርስ ጦርነት እያገገመች ባለችው ትግራይ የጦር መሳሪያ ንግድ እና ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር እንዳለ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ጌታቸው ረዳ ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ እሮብ ጳጉሜ 1/2015 ዓ.ም. በመቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ከትግራይ-ባህር ዳር፤ ደሴና ሰመራ የጦር መሳሪያ የሚያዘዋውሩ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው በክልሉ የሌብነት ወንጀል እጅግ ተንሰራፍቶ እንደሚገኝም ጨምረው ተናግረዋል።