ሲንጋፖር ዕጸ ፋርስ አዘዋውሯል ያለችውን ግለሰብ በሞት ልትቀጣ ነው

ታንጋራጁ ሱፒያህ

የፎቶው ባለመብት, TRANSFORMATIVE JUSTICE COLLECTIVE

ታትሟል

ሲንጋፖር እፀ ፋርስ (ካናቢስ) አዘዋውሯል ያለችውን ግለሰብ በስቅላት ልትቀጣ ነው።

ውሳኔው በበርካቶች ዘንድ አወዛጋቢ ሆኗል።

ተሟጋቾች ታንጋራጁ ሱፒያህ የተፈረደበት ያለ በቂ ማስረጃ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ባለሥልጣናት በበኩላቸው ክሱ በተገቢው ሒደት ማለፉንና ፍርዱን ረቡዕ ለመፈፀም ቀጠሮ መያዙን ተናግረዋል።

በሲንጋፖር ባለፈው ዓመትም የአዕምሮ ጤና ችግር ያለበት ግለሰብ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተያያዘ በሞት ተቀጥቷል።

ሲንጋፖር በዓለም ከባድ የሚባል የፀረ አደንዛዥ እፅ ሕግ ያላት አገር ናት።ሕጉ ማኅበረሰቡን ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ትላለች።

በቅርብ ቀናት የታንጋራጁ ቤተሰቦች እና ተሟጋቾች ለሲንጋፖር ፕሬዚደንት ሀሊማህ ያዕቆብ ደብዳቤዎችን በመላክ ምህረትን ተማፅነዋል። እንግሊዛዊው ቢሊየነር ሪቻርድ ብራንሰንም የሞት ፍርዱን እንዲያግዱ እና ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከቱት ጠይቀዋል።

የታንጋራጁ እህት ሊላ ሱፒያህም “ ወንድሜ ምንም ስህተት እንዳልሰራ አውቃለሁ። ፍርድቤቱ ጉዳዩን ከሥር መሠረቱ ጀምሮ እንዲመለከተው አሳስባለሁ" ስትል ለጋዜጠኞች ተናግራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የ46 ዓመቱ ታንጋራጁ ፍርዱ የተላለፈበት እንደ አውሮፓውያኑ በ2013 አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን ካናቢስ ከማሌዥያ ወደ ሲንጋፖር በማዘዋወር ሂደት ተሳትፏል በሚል ነው።

ምንም እንኳን አደንዛዥ እፁን ሲያቀርብ እጅ ከፍንጅ ባይያዝም፣ አቃቤያነ ሕግ በማስተባበሩ እንደተሳተፈ እና አደንዛዥ እፁን ያደረሰው ግለሰብ ጋር ስልክ የተለዋወጡበትን ሁለት የስልክ ቁጥሮች ሲከታተሉ እንደነበር ገልጸዋል።

ታንጋራጁ ግን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ከሌሎች ጋር ግንኙነት ሲያደርግ የነበረው እርሱ እንዳልሆነ ተናግሯል።

አቃቤያነ ሕጉ ከጠቀሷቸው ስልክ ቁጥሮች ውስጥ አንዱ ቀድሞ እንደጠፋውና የሁለተኛውም ባለቤቱ እርሱ እንዳልሆነ አስረድቷል።

የሲንጋፖር ሕግ በአደገኛ አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ላይ የሞት ቅጣትን፣ተባባሪዎች ላይ ደግሞ አነስተኛ ቅጣትን ይደነግጋል።

በታንጋራጁ የመጨረሻ ይግባኝ፣ ዳኛው ታንጋራጁ አደንዛዥ እፁን ወደሚፈለገው ቦታ በማዘዋወር ሒደቱ ላይ በማስተባበር ተሳትፎ እንደነበረው ከአቃቤያነ ሕጉ ጋር መስማማታቸውን ገልጸው ፣ይህም ለቀላል ቅጣት ብቁ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል።

ተሟጋቾች በበኩላቸው የታንጋራጁ ቤተሰቦች ጠበቃ ማቆም ባለመቻላቸው የመጨረሻውን ይግባኝ የተሟገተው በራሱ በመሆኑ እንዲሁም አስተርጓሚ ስላልቀረበለት በፍርድ ሒደቱ ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የሲንጋፖር ባለሥልጣናትም ታንጋራጁ አስተርጓሚ ቀደም ብሎ አልጠየቀም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የሲንጋፖር የሞት ቅጣትን የሚቃወመው ቡድን፣ ትራንስፎርማቲቭ ጄስቲስ ኮሌክቲቭ (TJC) ቃል አቀባይ ኪርስተን ሃን፣ መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት በማስጠበቅ ስም ሰዎችን መግደል እንደ መብት እየቆጠረው ነው ሲሉ ውሳኔውን አውግዘዋል።

ሲንጋፖር በአደንዛዥ እፅ ላይ ያላት ጥብቅ ሕግ ከጎረቤት አገሮች የቅርብ ጊዜ እርምጃ ጋር የተጻረረ ነው።

ታይላንድ የካናቢስን ንግድ ሕጋዊ አድርጋለች።ማሌዥያም ለከባድ ወንጀሎች የሞት ቅጣትን አስገዳጅ ማድረግ አቁማለች።