በካላሽንኮቭ ቅርጽ የተሰራው የአደንዛዥ ዕጽ ማጨሻ የአውስትራሊያ ነዋሪዎችን አስደነገጠ

በጠመንጃ ቅርጽ የተሰራ ለአደንዛዥ ዕጽ መጠቀሚያነት የሚውል ማጨሻ (ቦንግ)

የፎቶው ባለመብት, NSW Police Force

ታትሟል

በአውስትራሊያ ኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ውስጥ በጠመንጃ ቅርጽ የተሰራ ለአደንዛዥ ዕጽ መጠቀሚያነት የሚውል ማጨሻ (ቦንግ) ይዞ የታየ ግለሰብ በነዋሪዎች ላይ ድንጋጤን ፈጠረ።

ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ ኤኬ-47 የተባለውን ካላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዞ ሲንቀሳቀስ ነበር የተባለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ ግን ፖሊስ የጦር መሳሪያ ነው የተባለው ነገር ለተለየ አላማ የሚውል መገልገያ ሆኖ ተገኝቷል።

ረቡዕ ምሽት ከሲድኒ ከተማ ሰሜን ምዕራብ ከሚገኝ አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች ጠመንጃ ታጥቆ እየተንቀሳቀሰ ግለሰብን የሚመለከት በርካታ የስልክ ጥቆማ ለፖሊስ ይደርሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ የፖሊስ መኮንኖች እንዲሁም ሄሊኮፕተር ታጣቂውን ለመያዝ ወደ ስፍራው ተሰማርተው በደኅንነት ካሜራ በተቀረጸ መስል ድጋፍ አንድ ቆመ መኪና ጋር ይደርሳሉ።

ፖሊስ መኪናው ላይ ባደረገው ፍተሻም “ጠመንጃ” ያገኛል፤ ነገር ግን ጠመንጃው እውነተኛ የጦር መሳሪያ ሳይሆን ለአደንዛዥ ዕጽ ማጨሻነት በጠመንጃ ቅርጽ የተሰራ መገልገያ መሆኑን ተገንዝበዋል።

ከዚህ ነዋሪዎችን ካሸበረው ጉዳይ ጋር በተያያዘም አንድ የ50 ዓመት ዕድሜ ያለው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ፖሊስ ባወጣው መግለጫ “መኪናው ላይ በተደረገው ፍተሻ ክላሽንኮቭ ጠመንጃን የሚመስል መገልገያ ተገኝቷል። በሄሊኮፕተር ድጋፍም በአቅራቢያ ባለ በሳር በተሸፈነ መስክ ላይ አንድ ተጠርጣሪ ተይዟል” ብሏል።

ምንም እንኳን የተያዘው ጠመንጃ እውነተኛ መሳሪያ ባይሆንም፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋለው ግለሰብ ላይ ፈቃድ የሌለው የጦር መሳሪያ በመያዝ እና ነዋሪዎች ላይ ፍርሃት በመፍጠር ክስ ተመስርቶበታል።

ጉዳዩ በሚቀጥለው ሳምንት በፍርድ ቤት እስኪታይ ድረስ ተጠርጣሪው በእስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል።

የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የተያዘው ጠመንጃ መሳይ መገልገያ ውሃ ተሞልቶ ሃሺሽ እና ሌሎች ዕጾችን ለማጨስ ጥቅም ላይ እንደሚውል ፖሊስ ለፍርድ ቤት በሚያቀርበው ክስ ላይ ያስረዳል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት የዕጽ አጠቃቀም ሕግ እንደሚለው “የማጨሻ መገልገያውን ወይም የተወሰኑ ክፍሎቹን የተከለከሉ እጾችን ለመጠቀምም ሆነ ለሌላ ጉዳይ መሸጥ፣ ማቅረብ ወይም ለሽያጭ ማቅረብ” በወንጀል ያስጠይቃል።

ይህ የአደንዛዥ ዕጽ ማጨሻ መገልገያ የተሰራበት ኤኬ-47 የተባለው ክላሽንኮቭ ጠመንጃ በዓለም ዙሪያ በስፋት በርካሽ የሚገኝ እና ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሳሪያ ነው።

ኤኬ-47 በአውሮፓውያኑ በ1940ዎቹ ሚኻይል ካላሽንኮቭ በተባለ ግለሰብ ለሶቪየት ኅብረት ጦር ዲዛይን የተደረገ አውቶማቲክ የጦር መሳሪያ ነው።