ከ3 ሺህ ዓመታት በፊት ሰዎች አደንዛዥ ዕፅ ይወስዱ እንደነበር ጥናት ጠቆመ

ስፔን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከ3 ሺህ ዓመታት በፊት በስፔን አነቃቂና አደንዛዥ ዕጾች ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር አዲስ ጥናት ጠቆመ።

ሳይንቲስቶች በሜኖርካ በሚገኝ ጥንታዊ መካነ መቃብር ላይ የጸጉር ናሙና በመውሰድ ባደረጉት ጥናትም ነው ይህንን ያስታወቁት።

በዚህም መሰረት ጥንታዊ የሰው ልጅ ስልጣኔዎችና ከዕጽዋትና ከቁጥቋጦዎች የተገኙ አነቃቂና አደንዛዥ ዕጾችንም ይጠቀሙ እንደነበር አረጋግጠዋል።

አደንዛዥ ዕጾችን የሰው ልጅ መቼ ነው መውሰድ የጀመረው ለሚለውም፣ ይህ ግኝት በአውሮፓ ጥንታዊው ቀጥተኛ ማስረጃ እንደሆነ ይታመናል።

በሳይንቲፊክ ሪፖርቶች ጆርናል ላይ የታተመው ግኝት በደቡብ ምዕራብ ሜኖርካ በሚገኘው ኤስ ካሪትክስ ዋሻ ውስጥ የሰዎች እንቅስቃሴ እንደነበር ምልክቶችን አሳይቷል።

ዋሻው ከ200 በላይ መካነ መቃብሮችን የያዘ ሲሆን ለ600 ዓመታተ ያህል እስከ 800 ዓመተ ዓለም ድረስ የአምልኮ ስርዓት የሚፈጸምበት እና የቀብር ስፍራ ሆኖ ስለማገልገሉም ይታመናል።

ተመራማሪዎቹ እንደጠቆሙት ሰዎቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ንጥረ ነገሮች በጣም ጠንካራ ሲሆኑ በዋሻው ውስጥ በሚደረጉ የአምልኮ ስርዓቶችም አንድ አካል ሊሆኑ ይችላሉ።

የእነዚህንም ዕጾችን የጎንዮሽ ጉዳት መቆጣጠርም እንዲችሉ የአምልኮ መሪዎችም ተካተውበት ሊሆን እንደሚችልም አትተዋል።

በጥንታዊው የአምልኮ ስርዓቶች ላይ እንደቀለሙ የታመኑ የጸጉር ጉንጉኖች መሰረት ሶስት ሳይኮአክቲቭ (አነቃቂ) ንጥረ ነገሮች ተገኝተዋል።

ጉልበት፣ ብርታትና ንቃትን የሚጨምሩ እንዲሁም የሚያደነዝዙ ንጥረ ነገሮችንም በነዚሁ ስፈራዎች ውስጥ ስለመገኘታቸው ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዋሻው ውስጥ የተቀረጹና ጠመዝማዛ ምስሎች ያሏቸው ዕቃዎች መገኘታቸውንም ተመራማረዎች ጠቁመዋል። አንዳንድ ምሁራን ይህ በአደንዛዥ ዕጾች ስር ያለ ሰውን “የተቀየረ የንቃተ ህሊና ሁኔታን እንደሚወክል” አድርገው ይመለከቱታል ብለዋል።

ቀደም ሲል በአውሮፓ ውስጥ የቅድመ ታሪክ መድኃኒት አጠቃቀምን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አደንዛዥ ዕጾች በስዕሎች ላይ መታየታቸው ነበር።