በዩኬ በደረሰ የባቡር አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
በዩናይትድ ኪንግደም ቤድሮርድ አቅራቢያ በደረሰ የባቡር አደጋ 28 ሰዎች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን ዘጠኝ ሰዎች ለሕይወታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ፖሊስ አስታወቀ።
አርብ ዕለት ወደ ለንደን የሚያቀኑ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው አንድ የባቡር ሹፌር ሕይወቱ ሲያለፍ 100 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
አንደኛው ባቡር ከከርቢ የተነሳ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከኖቲንግሀም ወደ ለንደን ሴንት ፓንክረስ እየተጓዙ የነበሩ ናቸው።
የተሳፈሩበት ባቡር የተጋጨው ዶ/ር ፒተር ናፕ ከፊተኛው ክፍል ተቀምጠው እንደነበር ተናግረዋል።
"ስነሳ ሁሉም ወንበሮች በሁሉም ቦታ ተበታትነው ተመለከትኩ። የቦንብ ፍንዳታ ውስጥ ያለሁ ያህል ነበር የተሰማኝ" ብለዋል።
"ስነሳ የሰዎችን በደም የተሸፈነ ፊት እና የሰዎች እግር ተሰብሮ እና በሁሉም ቦታ ጭስ ተመለከትኩ።"
ሾላ ሚን በበኩሏ "ሰዎች ከወንበራቸው ወደ አየር እየበረሩ ነበር" ብላለች።
"በጣም ብዙ ደም ነበር። በርካታ ሰዎች የፊት ጉዳት ደርሶባቸዋል" በማለት ሁኔታውን ገልፃለች።
የልደት በዓል ለማክበር ወደ ለንደን እየተጓዘች እንደነበር የተናገረችው ተሬሳ ኢትባር "የቤድፎርድ ጣቢያን አለፍን፤ ከዚያም ግዙፍ ግጭት ተከሰተ። . . . ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላወቅኩም። ከፊቴ የነበረው ወንበር ራሴን መታኝ" ብላለች።
"ዓይኔን ስከፍት ነው ሰዎች ወለሉ ላይ ወድቀው፤ ደም በየቦታው ያየሁት።"
የብሪታኒያ የትራንስፖርት ፖሊስ አዛዥ ኮንስታብል ሉሲ ዶኦሪስ ቅዳሜ ዕለት በአደጋው አካባቢ እንዳሉ ግጭቱ እየተመረመረ እንደሆነ እና ሰዎች ከዘፈቀደ ግመታ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
ከቤድፎርድ የሚነሱ እና ወደ ቤድፎርድ የሚያቀኑ ባቡሮች በሳምንቱ መገባደጃ ቀናት አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል።
የትራንስፖርት ፖሊስ አዛዧ በአደጋው የመጀመሪያ ጥሪ የተቀበሉ የጤና ባለሙያዎችን "በአሳዛኝ እና ከባድ ሁኔታ ውስጥ ለሰሩት ግሩም ሥራ" እንዲሁም የአካበቢው ነዋሪዎች መሄጃ ላጡ እና ጉዳት ለደረሰባቸው መንገደኞች ላሳዩት ደግነት አመስግነዋል።
በርካታ አምቡላንስ ሂሊኮፕተሮች፣ ተሽከርካሪዎች እና 70 የእሳት አደጋ ሠራተኞች አደጋው እንደደረሰ በፍጥነት ተሰማርተዋል።
የባቡር አገልግሎቱ ኃላፊ ዊል ሮጀርስ በአደጋው ለተጎዱት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለማቅረብ የባቡር እና የድንገተኛ አገልግሎት ሠራተኞች እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
"ለባቡር ማኅበረሰቡ በጣም አሳዛኝ ቀን ነው" ብለዋል።
የዩኬ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሄይዲ አሌክሳንደር የግጭቱ እና የሞቱ ሰዎች ዜና በጣም እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
"ይህ ግጭት እንዴት እንደተፈጠረ ለማወቅ እና በድጋሚ እንዲህ ዓይነት አደጋ እንዳይገጥመን ለመማር ሰፊ ምርመራ እናደርጋለን" ብለዋል።
"የዩኬ የባቡር መስመሮች በዓለም ደኅንነቱ ከተጠበቁት መካከል ነው" ያሉት ሚኒስሯ፤ "እንዲህ ዓይነት አደጋ መድረሱ እንግዳ ነው" ሲሉ አክለዋል።












