ትራምፕ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በመተላለፍ ከካሊፎርኒያ ወደ ፖርትላንድ ወታደሮችን ላኩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፖርትላንድ የብሔራዊ ዘብ አባላትን ለማሰማራት ያደረጉት ሙከራ በፍርድ ቤት ውድቅ ከተደረገ በኋላ የፌደራል ወታደሮችን ከካሊፎርኒያ ወደ ኦሪጎን ላኩ።

የወታደሮቹ መላክ በፖርትላንድ ወታደሮች እንዳይሰማሩ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ውሳኔ የሚጥስ ነው ተብሏል።

የካሊፎርኒያ አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሶም "አስደንጋጭ የሆነ ሕግን እና ሥልጣንን ያለ አለግባብ መጠቀም" ሲሉ የጠሩትን የፕሬዚዳንቱን ተግባር በመቃወም ክስ እንደሚመሰርቱ ተናግረዋል።

በዲሞክራቶች የምትተዳደረዋ ፖርትላንድ ፕሬዚዳንቱ ወንጀልን መከላከል ሲሉ የጠሩት ዘመቻ አካል ሆናለች።

በከተማዋ ከሰነድ አልባ ስደተኞች ጋር በተያያዘ በቀጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወታደሮች ከተሞቹን ወደ ሰላም ለመመለስ አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ይከራከራሉ።

ፔንታጎን 200 የካሊፎርኒያ ብሔራዊ ዘብ አባላት "የዩኤስ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ማስፈጸሚያዎችን እና ሌሎች ይፋዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ የፌዴራል ሠራተኞችን ለመደገፍ" ወደ ፖርትላንድ መመደባቸውን አረጋግጧል።

የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አቢጌል ጃክሰን "ፕሬዚዳንት ትራምፕ በፖርትላንድ ውስጥ አመጽ የተቀላቀለበት ሁከት እና በሕግ አስከባሪ አካላት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ በፖርትላንድ የሚገኙ የፌዴራል ንብረቶችን እና ሠራተኞችን ለመጠበቅ ሕጋዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመዋል" ብለዋል።

የግዛቱ አስተዳዳሪ ኒውሶምን ደግሞ "ፖርትላንድን እና በመላ አገሪቱ ያሉ ከተሞችን ከሚያጠፉ አደገኛ ወንጀለኞች ይልቅ ሕግን ከሚያከብሩ ዜጎች ጎን መቆም አለበት" በማለት ወርፋቸዋለች።

ከጥቂት ወራት በፊት በሎስ አንጀለስ ሰነድ አልባ ስደተኞቸን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገ ሙከራ ወቅት በየዕለቱ ከፍተኛ የሆነ የተቃውሞ ሠልፍ መካሄዱ ይታወሳል።

በሰኔ ወር ዶናልድ ትራምፕ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማስቆም የብሔራዊ ዘብ አባላትን አሰማርተው ነበር።

እንዲህ ዓይነት የብሔራዊ ዘብ አባላትን የማሰማራት ኃላፊነት የግዛት ገዢው ነው።

ኒውሶም በሎስ አንጀለስ ወታደር መጠቀም አላስፈላጊ እና ውጥረትን የሚያባብስ ነው ሲሉ ተከራክረዋል። ትራምፕ በበኩላቸው ከተማዋን ከውድመት ታድጊያታለሁ ብለዋል።

የትራምፕ አስተዳደር በሎስ አንጀለስ የነበሩትን እነዚያኑ ወታደሮች ነው ወደ ፖርትላንድ ያሰማሯቸው።

ኒውሶም ትራምፕ ወታደሮቹን ወደ ፖርትላንድ ከላኩ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ፍርድ ቤቶችን ቸል ብለዋል ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

"ይህ የሕዝብ ደኅንነት ሳይሆን የሥልጣን ጉዳይ ነው። ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካን ጦር በአሜሪካ ዜጎች ላይ እንደ የፖለቲካ መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው" ብለዋል።

አክለውም "ይህን ወደ ፍርድ ቤት ወስደን አንሞግተዋለን። ነገር ግን ሕዝቡ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት እንዲህ አይነት ግድየለሽነት እና አምባገነንነት ሲፈፀም ዝም ማለት አይችልም።"

የትራምፕ አስተዳደር አጠናክሮ የቀጠለውን ሰነድ አልባ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር በመቃወም በፖርትላንድ እና በሌሎች ከተሞች ተቃውሞዎች ቀጥለዋል።

ወታደሮቹ ወደ ፖርትላንድ የተላኩት ትራምፕ 300 ብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ወንጀል ነው ያሉትን ለመቆጣጠር ወደ ቺካጎ ለማሰማራት ፈቃድ ከሰጡ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።