የኢስታንቡል ከንቲባ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመዝለፍ እስር ተበየነባቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኢስታንቡል ከንቲባ በንግግራቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመዝለፋቸው የእስር ቅጣት ተጣለባቸው።
በስድብ ጥፋተኛ ያደረጋቸው የቱርክ ፍርድ ቤት የሁለት ዓመት ተኩል እስር በይኖባቸዋል።
ኢክሬም ኢማሞግሉ በ2019 የነበረውን የአካባቢ ምርጫ የሻሩት “ሞኞች” ናቸው ማለታቸውም ነው ያስከሰሳቸው።
የ52 ዓመቱ ኢማሞግሉ የገዥውን ፓርቲ ኤኬ እጩ ተወዳዳሪን በማሸነፍ ነበር የከተማዋን ከንቲባነት ሥልጣን የተቆናጠጡት።
በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው በፖለቲካ ሥልጣናቸው እንዳይቀጥሉ ወይም በሚቀጥለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ ሊያደርጋቸውም ይችላል።
ከንቲባው ከሃይማኖት ገለልተኛ የሆነው የሪፐብሊካን ሕዝቦች ፓርቲ አባል ናቸው።
ፓርቲያቸው በመጪው ዓመት በሚካሄደውም ምርጫ ፕሬዚዳንት ኤርዶዋንን የሚገዳደር ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከንቲባው ይህንን አስተያት የሰጡት የከተማውን አስተዳዳሪነት ምርጫ በጠባብ ውጤት ካሸነፉ በኋላ ነው።
የኤኬ ፓርቲ በምርጫው ላይ መጭበርበሮች ነበሩ በሚል ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎም ነው የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ምርጫው በድጋሜ እንዲካሄድ ያዘዘው።
ኢማሞግሉ የመጀመሪያውን ምርጫ ውጤት የሻሩትን ለመግለጽ “ሞኞች” የሚለውን ቃል መጠቀማቸውን ደግፈውም በመከራከር የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሊ ለሚጠቀሙት ተመሳሳይ ቋንቋ ምላሽ ነው ብለዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ በተደገመውም ምርጫ ከተፎካካሪያቸው 770 ሺህ ድምጽ ብልጫ በማግኘት በቱርክ ትልቋ ከተማ የ25 ዓመታቱን የገዥውን ፓርቲ የበላይነት እንዲያከትም አድርገውታል።
የረቡዕ ውሳኔ በይግባኝ ፍርድ ቤት የሚጸና ከሆነ ኢማሞግሉ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ ውድድር ውጪ ይሆናሉ ማለት ነው።
የፍርድ ቤቱ ብይን ከተሰማ በኋላ በሰጡት የቪዲዮ መግለጫ “ከሕዝቡ የተሰጠኝን ሥልጣን በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች መንጠቅ አይችሉም” በማለት ሂደቱን ውድቅ አድርገውታል።
ከንቲባው ሕዝቡ ድጋፉን እንዲያሳይ ጥሪ ማድረጋቸውንም ተከትሎ ደጋፊዎች በኢስታንቡል ምክር ቤት ሕንጻዎች አካባቢ ተሰስበስው “መንግሥት ይልቀቅ”፣ “እውነት፣ ሕግና ፍትሕ” ሲሉም ተሰምተዋል።












