ማንችስተር ዩናይትድ የሪያል ማድሪዱን አማካይ ካሴሚሮ በ70 ሚሊዮን ፓውንድ አስፈረመ

ካሴሚሮ
ታትሟል

ማንችስተር ዩናይትድ የሪያል ማድሪዱን ብራዚላዊ አማካይ ካሴሚሮ በ70 ሚሊዮን ፓውንድ ለማስፈረም ተስማማ።

የ30 ዓመቱ ተጫዋች ከ2013 ጀምሮ ለሪያል ማድሪድ ተጫውቷል።

በቆይታው ክለቡ ሦስት ጊዜ የላ ሊጋ ባለድል ሲሆን፣ አምስት ጊዜ ቻምፒዮንስ ሊጉን አሸንፏል።

ማንችስተር ዩናይትድ መጀመሪያ ላይ 50 ሚሊዮን ዩሮ ከከፈለ በኋላ ቀጣዩን 10 ሚሊዮን ዮሮ የሚከፍለው ተጫዋቹ ሲፈርም ይሆናል።

በፕሪሚየር ሊጉ የታችኛው ደረጃ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ የፊታችን ሰኞ በኦልድ ትራፎርድ ስቴድየም ሊቨርፑልን ይገጥማል።

ካሴሚሮ ከዩናይትድ ከፍተኛ ተከፋዮች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ክለቡ ያስፈረው አራተኛ ተጫዋት ሲሆን፣ ከሱ ቀድሞ አማካዩ ክርስችን ኤሪክሰን፣ ታይረል ማላሲያ እና ተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲነዝ ፈርመዋል።

ዩናይትድ የጁቬንቱሱን ኤድርያን ራቢዮት ለማስፈረም ቢሞክርም የተጫዋቹን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ስላልቻለ ዝውውሩ አልተሳካም።

ስሱ የሆነውን የዩናይትድ አማካይ ክፍተት ለመሸፈን በሚልም ክለቡ ፊቱን ወደ ካሴሚሮ አዙሯል።

ካሴሚሮ የፊታችን ሰኞ በሚደረገው ጨዋታ አይሳተፍም።

በክለቡ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ ግን መገመት ይቻላል።

ባለፈው የጨዋታ ዓመት በላ ሊጋው ከነበሩ አማካይ ተጫዋቾች አንጻር የተሻለ ብቃት አሳይቷል።

በስኬታማ ሁኔታ በመከላከል ብራዚላዊው ተጫዋች በዓለም አንደኛ ሲሆን ተንሸራቶ ኳስ በመቀማት ደግሞ የባርሴሎናውን ሰርጂዮ ቡስኬዌትስ ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል።

ሪያል ማድሪድ በተሻለ ሁኔታ እንዲያጠቃ በማስቻልም የተጫዋቹ ሚና ቀላል አልነበረም።

ወደ ባለጋራ ቡድን ክልል በሚሻገሩ ኳሶች ኳሶች አምስተኛ እንዲሁም በሊጉ አማካዮች መካከል ኳስ በማቀበል ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከ2014 እስከ 2015 በተውሶ በፖርቹጋሉ ፖርቶ ተጫውቷል።

ለሪያል ማድሪድ 222 ጊዜ ተሰልፎ 24 ጎሎች አስቆጥሯል።

ዩናይትድ የአራት ዓመት ስምምነት ሊያስፈርመው የወሰነው ችሎታውን ከግምት በማስገባት ነው።

በተለይም በቻምፒዮንስ ሊግ ያሳየው ብቃት ይጠቀሳል።

በስፔን ይከፈለው ከነበረው በዩናይትድ እጥፍ ይከፈለዋል ቢባልም በግልጽ አልተነገረም።

ዞሮ ዞሮ ከማንችስተር ዩናይትድ ከፍተኛ ተከፋዮች አንዱ ነው የሚሆነው።

የዩናይትድ አመራሮች ተጫዋቹን እንደሚያደንቁትና ለማስፈረምም ሲያስቡ እንደቆዩ ተሰምቷል።

እሱም ወደ ኦልድ ትራፎልድ የማቅናት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

አዲሱ አሠልጣኝ ኤሪክ ተን ሀግ የክለቡን ስሱ ቦታዎች እያጠናከሩ ይገኛሉ።

ሙያውን ማክበሩ፣ ብልህነቱና ጥንካሬው ክለቡን በአጭር ጊዜ ስኬታማ እንደሚያደርግ የማንችስተር ዩናይትድ አመራሮች ያምናሉ።