የአሜሪካን ምርጫ የሚወስነው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ እንደዘንድሮው ምርጫ ፉክክሩ ጦዞ አያውቅም።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ምርጫዎችን መለስ ብሎ ለሚያይ እኤአ በ2000 ጆርጅ ደብሊው ቡሽ በአል ጎር ላይ የተቀዳጁት ድል በፍሎሪዳ ባገኙት በትንሽ መቶዎች የሚቆጠር የአብላጫ ድምጽ እንደነበር ይረዳል።
በአሜሪካ ሁሌም ምርጫው ለማን ያዘነበለ እንደሆነ የሚታወቅበት ዕድል አለ።
በአውሮፓውያኑ 2016 የተካሄደው ምርጫ ላይ ግን ይህ ግምት የተዛባ ሆኖ ተገኝቷል።
በዚያ ዓመት የመራጮችን አስተያየት የሚገምቱ ሁሉ ዕድል ፊቷን ወደ ሒላሪ ክሊንተን ታዞራለች ሲሉ ተንብየው ነበር።
በኋላ እንደታየው ግን ዶናልድ ትራምፕ አሸናፊ ሆነው ወጥተዋል።
በአሁኑ ምርጫ ግን የምርጫው ውጤት ለሁለቱም ያደላ መሆኑን የሚያሳዩ ትንበያዎች በርካታ ናቸው።
ማንም ደፍሮ አንዱ ያሸንፋል ሊል አልቻለም።
ለገማች ያስቸገረው ምርጫ
የምርጫውን ውጤት በአገር አቀፍም ሆነ ወሳኝ በሆኑት ሰባት ግዛቶች የሚገምቱ ሁሉ ለሁለቱም ተፎካካሪዎች ተቀራራቢ ግምት ይሰጣሉ።
ይህ እርግጠኛነት ያልታየበት ትንበያ ነው የፖለቲካ ተንታኞችን እና የምርጫ ዘመቻ ባለሙያዎችን እንዲወላውሉ ያደረጋቸው።
እንደ አስረጅነትም ሪፐብሊካንን በመምረጥ በምትታወቀው የአዮዋ ግዛት ካማላ ሃሪስ እየመራች መሆኑን የሚያሳየው ግምት ምርጫውን በንቃት ለሚከታተሉ ሁሉ እጅን በአፍ ያስጫነ ጉዳይ ነበር።
ነገር ግን ዋና ዋና የምርጫ መላምት የሚያቀርቡም ሆኑ ውጤቱን የሚተነብዩ የሚስማሙበት የዚህን ምርጫ ውጤት ማገመት አስቸገሪ መሆኑን ነው።
ምርጫውን በአብላጫ ድምጽ ማሸነፍ ይቻላል?
የዚህን ምርጫ አሸናፊ ቀድሞ ማወቅ አዳጋች ስለሆነ ብቻ አንዱ ዕጩ በአብላጫ ድምጽ አያሸንፍም ማለት አይደለም።
ብርቱ ፉክክር በሚደረግባቸው ግዛቶችም ሆነ በሌሎች ዕጩዎች ሙሉ በሙሉ ሊያሸንፉ የሚችሉበት ዕድል አለ።
በዚህ ምርጫ ላይ የዜጎች ተሳትፎ ላይ የቀረበው የእስካሁን ግምት ስህተት ከሆነ እና በርካታ ሴት መራጮች፣ ወይንም ደግሞ በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች፣ በርካታ ወጣት መራጮች ለመምረጥ የሚወጡ ከሆነ የዚህን ምርጫ የመጨረሻ ውጤት የመቀየር ዕድል ይኖራቸዋል።
ወሳኝ በሆኑ የመራጮች ቡድን ውስጥ ያልታሰበ ውጤት ሊከሰት ይችላል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ዘመቻው እንደተገመተው ጥቁር እና የላቲን ዝርያ ያላቸው ወጣቶችን መማረክ ከቻሉ፣ ካማላ ሃሪስ ቡድናቸው መገመት እንደቻለው ለረዥም ዘመናት ሪፐብሊካንን ሲመርጡ የነበሩትን ከተማ ቀመስ ሴቶችን ልብ ማማለል ከቻሉ አሸናፊ ይሆናሉ።
በተጨማሪም በዕድሜ የገፉ መራጮች ለዓመታት ድምጻቸውን ለሪፐብሊካን በታማኝነት ሲሰጡ ኖረው አሁን ወደ ዲሞክራቶች ጎራ አዘንብለው ከተገኙ የምርጫው ውጤት ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ።
ምርጫው ተጠናቅቆ ውጤት ማወቅ ሲጀመር አሸናፊው ዕጩ ለምን የበላይነቱን እንዳገኘ ለመናገር እነዚህ ነጥቦች ወሳኝ ይሆናሉ።
ምናልባትም ምርጫውን መለስ ብሎ ለሚቃኝ መልሱ ግልጽ ይሆናል።
ነገር ግን አሁን የአሜሪካ ምርጫን እንዴት አንደሚጠናቀቅ፣ ማን እንደሚያሸንፍ አውቃለሁ የሚል ዋሾ እሆናል።
ሁሉም ዓይናቸውን የጣሉባቸው ወሳኝ ግዛቶች
በአብዛኞቹ የአሜሪካ ግዛቶችን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ውጤት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ነገር ግን ይህንን ምርጫ የሚወስኑ ሰባት ግዛቶች አሉ።
ይኹን እንጂ ሁሉም ግዛቶች እኩል አይደሉም።
እያንዳንዱ ዕጩ ወደ ዋይት ሐውስ የሚያደርገውን ጉዞ ለመወሰን የሦስት ግዛቶች ድምጽ ወሳኝ ናቸው።
ለዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩዋ ካማላ ሃሪስ ፔንስልቬንያ፣ ሚቺጋን እና ዊስኮንሲን ወሳኝ ናቸው።
እ.ኤ.አ. በ2016 ትራምፕ በዲሞክራቲክ ፓርቲ ደጋፊነታቸው የሚታወቁት ሦስቱ ግዛቶችን በጠባብ ልዩነት ካሸነፉ በኋላ በፖለቲካው ዓለም ባሉ ሰዎች ዘንድ መነጋገርያ ሆነዋል።
በ2020 ጆ ባይደን የእነዚህን ግዛቶች ድምጽ ማግኘት ችለው ነበር።
ካማላ ሃሪስ እነዚህን ግዛቶች ማሸነፍ ከቻሉ፣ በኤሌክቶራክ ኮሌጅ የተለየ ሥርዓት የምትከተለዋን ኔብራስካን ከጠቀለሉ፣ ሌሎች የፉክክር መድረክ የሆኑ ግዛቶች ብዙ አያሳስቧቸውም።
ምርጫው ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ ለምን በእነዚህ ግዛቶች ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ለሚመለከት ጉዳዩ ግልጽ ይሆንለታል።
ሃሪስ ሰኞ ማታ የመጨረሻውን የምረጡኝ ቅስቀሳ በፊላደልፊያ እና በፔንስልቬንያ አድርገዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው ሰሜን ካሮላይና እና ጆርጂያ ላይ ዓይናቸውን ጥለዋል።
እነዚህን ግዛቶች የሚያሸንፉ ከሆነ በሌሎች ግዛቶች የሚሰጡ ድምፆች ምንም ሆኑ ምን ሁለት ኤሌክቶራል ድምጽ ያገኛሉ።
ባለፈው ሳምንት ውስጥ በሰሜን ካሮላይና አምስት የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻዎችን ያደረጉበት ምክንያትም ይኸው ነው።
ሁለቱም ተፎካካሪዎች ዓይናቸውን ያሳረፉበት ግዛት ፔንሴልቬንያም እንዲሁ በርካታ ኤሌክቶራል ድምጽ ያለው ግዛት ነው።
የአሜሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ
ካማላ ሃሪስ እና ትራምፕ በስደተኞች ጉዳይ፣ ንግድ፣ ባሕል እና የውጭ ጉዳይ ላይ ሁለት የተለያዩ አቋሞችን ያንጸባርቃሉ።
ለቀጣይ አራት ዓመታት የመሪነቱን መንበር የሚይዙት ሰው የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የወደፊቱ ትውልድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ የአሜሪካን መጻዒ ዕድልን ይቀርጻል።
ባለፉት አራት ዓመታት የአሜሪካ የፖለቲካ ገጽታ በሁለቱም ፓርቲዎች የመራጮች ስብጥርን በሚመለከት በፍጥነት ነው የተቀያየረው።
የሪፐብሊካን ፓርቲን የወከሉትን ዶናልድ ትራምፕን ለሚመለከት ከዚህ በፊት ከነበረው እና ከተለመደው በተለየ ሕዝበኛ የሆኑ መሪ በመመረጥ የተለየ አቋም አንጸባርቋል።
የዲሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ሕዝባዊ መሠረት አሁንም ወጣት እና የጥቁር እና ላቲን ዝርያ ባላቸው መራጮች እጅ የተወሰነ ቢሆንም ሀብታም እና የኮሌጅ ምሩቅ መራጮችም ተቀላቅለዋል።
ማክሰኞ የሚታየው ውጤት ደግሞ ባለፉት ስምንት ዓመታት ያልነበረው ይህ ለውጥ በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ለምን ሊታይ እንደቻለ የበለጠ መልስ ይሰጣል።












