ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በምርጫ እንዳይሳተፉ ታገዱ
የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ምርጫ ለፓርላማ አባልነት እንዳይወዳደሩ ከለከለ።
የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዙማ ችሎት በመድፈር የተፈረደባቸው የ15 ወራት እስራት ከምርጫው እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል ብሏል።
ዙማ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት እአአ በ2021 የሙስና ወንጀል ምርመራ ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው እስራቱ ተላልፎባቸው የነበረው።
ጃኮብ ዙማ ከአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ጋር በመጋጨታቸው ምክንያት አዲስ በተመሠረተው ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ (ኤምኬ) ፓርቲን ወክለው የምርጫ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።
የኤምኬ ዋና ፀሐፊ ሲህሌ ንጉባኔ ፓርቲው በውሳኔው ቅር ቢሰኝም የምርጫ ቅስቀሳውን አይጎዳውም ብለዋል።
“እሱ [ዙማ] አሁንም የፓርቲው መሪ ነው። ውሳኔው የእኛን ዘመቻ በምንም መልኩ አይጎዳውም” ብለዋል።
ንጉባኔ አክለውም የዙማ ስም በምርጫ ወረቀቱ ላይ እንደሚቆይ ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ምርጫ ደቡብ አፍሪካውያን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይመርጣሉ፣ ዕጩዎች ፓርቲው በሚያገኘው ድምጽ መሠረት የፓርላማ መቀመጫ ያገኛሉ።
ኤምኬ ወደ ፖለቲካ ምኅዳሩ ብቅ ማለቱ ኤኤንሲ የአፓርታይድ ሥርዓት ካበቃ ካለፉት30 ዓመታት ወዲህ የፓርላማውን አብላጫ መቀመጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያጣ ይችላል የሚል ግምት በዝቷል።
ኡምኮንቶ ዊሲዝዌ አፓርታይድን የታገለው የኤኤንሲ ወታደራዊ ክንፍ የመጀመሪያ ስም ነው።
ጃኮብ ዙማ ውሳኔውን በተመለከተ እስካሁን አስተያየታቸውን አልሰጡም።
ከሦስት ዓመት በፊት ዙማ እስር ሲፈረድባቸው ከባድ ረብሻ ፈጥረው የነበረ ሲሆን፣ አንዳንዶችም ፍርድ ቤት ዙማን ከምርጫው ውጪ የሚያደርጋቸው ከሆነ አደገኛ ተቃውሞ እንደሚቀሰቅሱ አስጠንቅቀው ነበር።
ነገር ግን የዙማ ፓርቲ መሪዎች ይህንን ሃሳባቸውን በመቀየር ትኩረታቸውን የምክር ቤቱን አብላጫ ሁለት ሦስተኛ መቀመጫ ላይ በማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አድርገው ዙማን ወደ ሥልጣን እንዲመለሱ የማድረግ ዕቅድ አላቻው።
የፍርድ ቤት ዕግድ ውሳኔውን ተከትሎ የዙማ ጠበቆች ከሦስት ወራት እስር በኋላ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እንዲለቀቁ በማድረጋቸው ቅጣቱ ሙሉ ለሙሉ ተሰርዟል በማለት ተከራክረዋል።
ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ዙማ በእስር ያሳለፉት የጊዜ ርዝመት ለአሁኑ ውሳኔ አስፈላጊ አይደለም በማለት የጠበቆቻቸውን ክርክር ሳይቀበለው ቀርቷል።
የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት የአገሪቱን “ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት” ተዓማኒነት ለመጠበቅ በሚል ለ12 ወራት እስር የተፈረደበት ማንኛውም ሰው ተመርጦ ወደ አገሪቱ ፓርላማ እንዳይገባ ይከለክላል።