ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰባት ጨቅላዎችን የገደለችው እንግሊዛዊት ነርስ የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነባት
በእንግሊዝ ጨቅላዎችን በመግደል ጥፋተኛ የተባለችው ሉሲ ሌንትባይ ቀሪ የሕይወት ዘመኗን በእስራት እንድታሳልፍ ውሳኔ ተሰጥቶባታል።
የ33 ዓመቷ ነርስ ከምትሰራበት ሆስፒታል ውስጥ ሰባት ጨቅላዎችን በተለያየ ሁኔታ መግደሏ ባለፈው ዓርብ በዋለ ችሎት ተረጋግጧል።
ሌሎች ስድስት ሕጻናትንም ለመግደል መሞከሯ የተረጋገጠ ሲሆን በመመረዝ፣ የተበከለ ወተት በመስጠት እና በኃይል በመጫን ነው ሕጻናቱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረችው ተብሏል።
ሉሲ የቀረበባትን ክስ ለመስማት ፍርድ ቤት አልቀርብም በማለት ችሎቱን ሳትታደም ቀርታለች።
በመሆኑም በሌለችበት ዳኛው ብያኔ ሰጥተዋል። ሉሲ ብዙ የዕድሜ ልክ እስራት ብያኔዎች የተላለፉባት ሲሆን አንደኛው በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ በአራት ሴቶች ላይ ብቻ የተሰጠ ብያኔ ሲሆን አራተኛዋ ሉሲ ሌትባይ ሆናለች።
በዩናይትድ ኪንግደም የዕድሜ ልክ እስራት እጅግ ለከፋ ወንጀል የሚሰጥ የመጨረሻው ብያኔ ነው።
“ሰው በተፈጥሮው ለሕጻናት ከሚያደርገው እንክብካቤ እና ፍቅር ተቃራኒ የሆነ ነገር ነው የፈጸምሽው። ከዚያም ባለፈ ሁሉም ዜጋ በጤና ዙሪያ የሚሰሩ ሙያተኞች ላይ የሚጥለውን ዕምነት ያረከሰ ተግባር ፈጽመሻል” ብለዋል ዳኛው።
ዳኛው አክለውም “የሰራሽውን አስቀያሚ ድርጊት ማመን እና መጸጸት አልፈለግሽም። በዚህም ምክንያት የተጣለብሽን ውሳኔ ለማቅለል ምንም ምክንያት የለም” ብለዋል።
ውሳኔው በተሰጠበት ወቅት የሉሲን ጉዳይ ለስምንት ወራት ሲከታተሉ የነበሩት ሁሉም 10 ዳኞች ተገኝተዋል። አንዳንዶቹ ልጆቻቸው የተጎዱባቸው ቤተሰቦችን ሃዘን በመመልከት ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉ ፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር።
የፍርድ ውሳኔው ሲሰማ ቤተሰቦች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በለቅሶ ይንሰቀሰቁ ነበር።
በሌሎች የፍርድ ሂደቶች ይገኙ የነበሩት የሉሲ ቤተሰቦች የመጨረሻው ውሳኔ በሚሰጥበት ወቅት ፍርድ ቤት አልተገኙም።
ልጆቻቸው የተገደሉባቸው ወላጆች ግን በስፍራው ተገኝተው “አረመኔያዊው የነርሷ ተግባር ዕድሜ ዘመናችንን የማንረሳው ጠባሳ አሳርፎብናል” ብለዋል።
የተጎጅ ቤተሰቦችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች የሉሲ ሌትባይን ፍርድ ቤት ለመቅረብ አሻፈረኝ ማለት በብርቱ ተችተዋል። “ከበደለቻቸው ሰዎች ፊት ቆማ ፍርዷን መስማት ነበረባት” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የፍትህ ሚንስትር አሌክስ ቻክ በትዊተር [ኤክስ] ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ሉሲ ሌትባይ ገዳይ ብቻ ሳትሆን ፈሪም ናት። የተጎጅ ቤተሰቦችን የጉዳት ስሜት እና የህዝቡን ቅሬታ ለመስማት ፊት ለፊት መቅረብ አለመቻል የመጨረሻው የስድብ አይነት ነው” ብለዋል።
“ጥቃት ፈጻሚዎች ተገደው ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው ጥፋታቸውን እንዲሰሙ እና ጉዳት ያደረሱባቸውን ሰዎች ሁኔታ እንዲመለከቱ በቀጣይ ሕጉን እንቀይረዋለን” ብለዋል ሚንስትሩ።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ሪሺ ሱናክም ፍርድ ቤት ቀርቦ በራስ ላይ የሚወሰንን ብያኔ አለመስማት እና የተጎጅ ቤተሰቦችን ለማየት አለመድፈር የፈሪነት መገለጫ ነው ብለዋል።
ሉሲ በምትሰራበት ሆስፒታል ጉዳት እያደረሰች መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ለሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ መቅረብ የጀመሩት ከ8 ዓመት በፊት በፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ ነው። ነገር ግን ወዲያውኑ እርምጃ ባለመወሰዱ መረጃው ለሃላፊዎች ከደረሰ በኋላም በአምስት ልጆች ላይ ጉዳት ሲደርስ ሁለቱ ሞተዋል።
ሉሲ ታደርሳቸዋለች የተባሉ ጥቃቶች እየጨመሩ ሲመጡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ከስራ ተሰናብቷል። የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ሚንስቴርም “ውሳኔው የተላለፈው የወንጀል ምርመራውን ተከትሎ ነው” ብሏል።