ለተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ጸሎት ከተፈቀደ በኋላ የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያን መሪ ተወገዙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእንግሊዝ ቤተክርስቲያን ለተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ጸሎት እንዲደረግ ድጋፍ ከሰጠች በኋላ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ የአንግሊካን መሪዎች የቤተ ክርስቲያኗ መሪ ጀስቲን ዌልቢ መሪያችን አይደሉም አሉ።
በመላው ዓለም የሚገኙት እና 42 አባላት ካሉት የአንግሊካን ኅብረት አባላት መካከል አሥሩን የሚወክሉት ሊቀ ጳጳሳት፤ ጀስቲን ዌልቢ ከአሁን በኋላ “የዓለም አቀፉ ኅብረት መሪ” አድርገን አንመለከታቸውም ብለዋል።
ሊቀ ጳጳሳቱ ጨምረውም የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያን “እናት ቤተ-ክርስቲያን” ከመሆን “ውድቅ” ተደርጋለች ብለዋል።
የካንተበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው አብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት ሲያጡ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
42 አንግሊካን አብያተ ክርስቲያናትን ያቀፈው ዓለም አቀፉ የአንግሊካን ኅብረት እአአ 1867 በእንግሊዝ አገር ከተመሠረተ ጀምሮ የካንተበሪ ሊቀ ጳጳሳት የኅብረቱ መንፈሳዊ መሪ ኃላፊነትን ሲወስዱ ቆይተዋል።
የካንተበሪ ሊቀ ጳጳሳት በኅብረቱ ላይ ይፋዊ ሥልጣን ባይኖራቸውም ‘የሞራል ኃላፊነት’ ያላቸው ሲሆን፣ የሊቀ ጳጳሳት ‘አውራ’ ተደርገውም ይወሰዳሉ።
የሊቃነ ጳጳሳቱን ተቃውሞ ተከትሎ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ይፋዊ መኖሪያ የሆነው ላምቤዝ ቤተ-መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ በዓለም አቀፉ የአንግሊካን ኅብረት አስተዳደር ላይ ለውጥ አይኖርም ብሏል።
10 ሊቃነ ጳጳሳት እና በአሜሪካ እና ብራዚል የሚገኙ ሁለት ተገንጣይ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያን ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው ሰዎችን ለማጋባት እና ለጋብቻ ጸሎት መፍቀዷን የተቃወሙት።
ውሳኔውን የተቃወሙት የደቡብ ሱዳን፣ የቺሊ፣ የኢንዲያን ኦሽን፣ የኮንጎ፣ የሚያንማር፣ የባንግላዴሽ፣ የኡጋንዳ፣ የሱዳን፣ የአሌክሳንደሪያ እና የሜላኔሲያ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በተለይ በእሲያ እና በአፍሪካ ብዙ ተከታዮች ያሏቸው ናቸው።
ተቃውሟቸውን ያሰሙት ሊቃነ ጳጳሳት ባወጡት መግለጫ ላይ የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያን በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጸንተው ከሚገኙት የኅብረቱ አባላት ለመለየት ወስናለች ብለዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጀስቲን ዌልቢ የምትመራው የእንግሊዝ ቤተ-ክርስቲያን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ለሚፈጽሙ ጸሎት እንዲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቃድ ሰጥታ ነበር።
ይሁን እንጂ አሁንም ቤተ-ክርስቲያኗ በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ላይ ያላት አቋም አልተቀየረም እንዲሁም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ማድረግ አልተፈቀደም።












