በናይጄሪያ በሞተር ሳይክል በታገዘው የወንበዴዎች ጥቃት ከ200 በላይ ሲቪሎች ተገደሉ

ማንነታቸው የማይለይ ጦር መሳሪያ ያነገቡ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሰሜን ምዕራባዊ ናይጄሪያ ዛምፋራ ግዛት ውስጥ ሞተረኛ የታጣቂ ቡድን አባላት ለቀናት በሰነዘሩት አሰቃቂ ጥቃት የበርካቶችን ሕይወት አጠፉ።

በአካባቢው እስካሁን ቢያንስ የ200 ሰዎች የቀብር ስነ-ሰርዓት ተፈጽሟል።

በሕይወት የተረፉ የአዓን እማኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሞተር ሳይክል ተጭነው የመጡት ታጣቂዎቹ በየመንደሩ እየዞሩ ያገኙት ሰው ላይ በመተኩስ ነው ጥቃቱን የፈጸሙት።

ጥቃቶቹ የተፈጸሙት ባለፈው ሳምንት መንግሥት ባደረገውን ወታደራዊ የአየር ድብደባ የታጣቂ ቡድን አባላትን መምታቱን ተከትሎ ነው።

ቡድኖቹ ዛምፋራ እና አጎራባች ክልሎችን ለበርካታ ዓመታት ሲያጠቁ ኖረዋል።

በአካባቢው ነዋሪዎች ሽፍቶች በመባል የሚታወቁት እነዚህ ቡድኖች፤ በየቦታው የሚንቀሳቀሱ፣ ብዙ ጊዜ እንስሳትን የሚዘርፉ፣ ሰዎቸን በማገት ማስለቀቂያ ገንዘብ የሚጠይቁ እና የሚጋፈጧቸውን ደግሞ የሚገድሉ የረቀቀ የወንጀለኞች መረብ የዘረጉ ናቸው።

በዚህ ሳምንት የናይጄሪያ መንግሥት ታጣቂዎች ላይ የጸጥታ ሃይሎች ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰዱ ለማስቻል አሸባሪ በማለት በይፋ ፈርጆ ነበር።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አርብ ዕለት ከ100 በላይ ሰዎች በታጣቂ ቡድኖች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፤ 300 የሚሆኑ በሞተር ሳይክል የታገዘ ጥቃት ያደረሱት ታጣቂ ቡድኖች ከማክሰኞ እስከ ሃሙስ ምሽት ድረስ ዘጠኝ የሚደርሱ ማህበረሰቦችን እየዞሩ ካጠቁ በኋላ የተወሰደ እርምጃ ነው።

ታጣቂዎች በጥቃቱ የነዋሪዎቹን መኖሪያ ቤቶች አቃጥለዋል እንዲሁም የተጎጂዎቻቸውን አካል ቆራርጠው መጣላቸውም ተዘግቧል።

ጥቃት ከተፈጸመባቸው መንደሮች በአንዱ ነዋሪ የሆነው ኢዲ ሙሳ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገረው አጥቂዎቹ ወደ 2,000 የሚጠጉ የቀንድ ከብቶችንም ዘርፈዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ጥቃቱን የፈጸሙት የታጠቁ ቡድኖች ወደ ምዕራባዊው የዛምፋራ ግዛት የመንግሥት ጥቃቶች በመሸሽ ሳሉ ነበር።

የሰብዓዊ ጉዳዮች ሚኒስተር ቃል አቀባይ ሳዲያ ኡመር ፋሩክ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ከ200 በላይ ሰዎች ቀብር ተፈጽሟል።

ከ10,000 የሚበልጡ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሸሻቸውን እና በርካቶች እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ተናግረዋል።

በአጎራባች ኬቢቢ ግዛት የሚገኙ ባለስልጣናት በሽፍታዎች ለስድስት ወራት ተይዘው የቆዩ 30 ተማሪዎችን እና አንድ መምህርን መልቀቃቸውን የገለጹ ሲሆን ለማስለቀቅ ገንዘብ ይከፈል አይከፈል የሚለው ግን ግልጽ አይደለም።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ መንግሥት ከ"ሕገ-ወጦች" ጋር በሚያደርገው ውጊያ አይጸጸትም ሲሉ ተናግረዋል።

"ወንበዴዎቹ በንፁሀን ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት ተስፋ ከመቁረጥ የመነጨ ነው። አሁን በወታደራዊ ኃይላችን ያላሰለሰ ትግል ጫና እየደረሰባቸው ነው" ሲሉ ፕሬዘዳንቱ ቅዳሜ ምሽት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የናይጄሪያ መንግሥት ሃይሎች ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ በክልሉ 537 "ታጣቂ ቡድኖች እና ሌሎች ወንጀለኞችን" መግደላቸውን እና ሌሎች 374 ሰዎችን ማሰራቸውን ባሳለፍነው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ የናይጄሪያ ወታደሮች ታጣቂዎቹን ለመውጋት ተሰማርተዋል።