አሜሪካ በአፍጋኒስታኑ ሕጻናት ጭምር ለሞቱበት የድሮን ጥቃት ወታደሮቼ ተጠያቂ አይሆኑም አለች

ታትሟል

ባለፈው ነሐሴ በአፍጋኒስታን ሕጻናትን ጨምሮ 10 ሰዎችን ለገደለው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት የአሜሪካ ወታደሮች ወይም ባለስልጣናት ተጠያቂ እንደማይሆኑ ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች።

ጥቃቱ የተፈጸመው ታሊባን ዋና ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ቡድን ካቡል ከተማን እየለቀቀ በነበረበት የመጨረሻ ቀናት ላይ ነው።

በጥቃቱ አንድ የእርዳታ ሠራተኛ እና ዘጠኝ የቤተሰቡ አባላት ህይወታቸው አልፏል፤ ሰባቱ ህጻናት ናቸው።

የአሜሪካ የስለላ ድርጅት የእርዳታ ሠራተኛው መኪና አይኤስ-ኬ ከተባለ በቀጠናው ከሚንቀሳቀስ የኢስላሚክ ስቴት ቡድን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምን ነበር።

በኋላ ላይ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ጄኔራል ኬኔት ማኬንዚ ነሐሴ 29 የተደረገውን ጥቃት "አሳዛኝ ስህተት" ሲሉ ገልጸውታል።

ባለፈው ወር የታተመ የግምገማ ውጤት ምንም ዓይነት ህግ ስላልተጣሰ የዲሲፕሊን እርምጃ አያስፈልግም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል። የስነ-ምግባር ጉድለት ወይም ቸልተኝነትም ጥሰት ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም ብሏል።

በርካታ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ግምገማው ሰኞ ዕለት በመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን መጽደቁን ዘግበዋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው አንድ አጥፍቶ ጠፊ ከካቡል አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ እስከ 170 የሚደርሱ ንፁሀን ዜጎች እና 13 የአሜሪካ ወታደሮች ከገደለ ከቀናት በኋላ ነው።

የአሜሪካ ሃይሎች የእርዳታ ሠራተኛ የሆነው ዛማይሪ አህማዲን መኪና ዒላማ ያደረጉ ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመው ከአየር መንገዱ 3 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መኪናው ይዞ ሲወጣ ነው።

ተሽከርካሪው ከአይኤስ-ኬ ጋር ግንኙነት ባለው ግቢ ውስጥ የታየ ሲሆን እንቅስቃሴዎቹ የሽብር ቡድኑ ለሌላ ጥቃት ካቀደው መረጃ ጋር የተጣጣመ ነበር።

ከፍንዳታው በኋላ ሁለተኛ ፍንዳታ የተከተለ ሲሆን ይህም የአሜሪካ ባለስልጣናት መጀመሪያ ላይ መኪናው ፈንጂዎችን መያዙን የሚያረጋግጥ ነው እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ይሁን እንጂ በምርመራው ምናልባት መንገድ ላይ በነበረ የጋዝ ሲሊንደር የተከሰተ ሊሆን ይችላል ተብሏል።