በዶክተር ላሪ ናስር ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴቶች 380 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ሊከፈላቸው ነው

በዶ/ር ላሪ ናስር ጾታዊ ትንኮሳ ከደረሰባቸው መካከል በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ ማካይል ማሮኒ (ግራ) እና ሲሞን ቢለስ ይገኙበታል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዶ/ር ላሪ ናስር ጾታዊ ትንኮሳ ከደረሰባቸው መካከል በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ ማካይል ማሮኒ (ግራ) እና ሲሞን ቢለስ ይገኙበታል፡፡
ታትሟል

በአሜሪካ የጂምናስቲክስ አሰልጣኝና ሐኪም በነበረው በዕውቁ ዶ/ር ላሪ ጄራርድ ናስር ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ከመቶ በላይ ሴቶች በታሪክ ከፍተኛ የተባለ የካሳ ክፍያ ሊሰጣቸው ነው፡፡

የአሜሪካ ብሔራዊ ጂምናስቲክ ፌዴሬሽን ቡድን ሐኪም የነበረው ዶ/ር ላሪ ናስር በበርካታ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ በፈጸመው ወሲባዊ ትንኮሳ በድምሩ 300 ዓመት እስር ተበይኖበት ማረሚያ ቤት ይገኛል፡፡

ይህንን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ለተጠቂዎች ለመክፈል የተስማማው በዋናነት የአሜሪካ ጂምናስቲክ ማኅበር ነው፡፡

ጉዳዩ ላለፉት አምስት ዓመታት በፍርድ ሂደት ተይዞ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ለተጎጂዎች በድምሩ 380 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል በመስማማቱ ተቋጭቷል፡፡

ዶ/ር ላሪ ናስር ለረዥም ዘመን የአሜሪካ የብሔራዊ ጂምናስቲክ ቡድን ሐኪምና አሰልጣኝ ነበር፡፡

ለበርካታ ዓመታት ሰልጣኝና ተወዳዳሪ ልጃገረዶችን ወሲባዊ ትንኮሳ ሲያደርስባቸው እንደኖረ ደፍረው ወደ አደባባይ የወጡ ሴት አትሌቶች ከብዙ ዓመታት ማቅማማት በኋላ አጋልጠዋል፡፡

ከጊዜ በኋላም በዶ/ር ላሪ ክስ ተመስርቶ በአገሬው አቆጣጠር በ2018 ዓ/ም ፍርድ ቤት ጥፋተኝነቱን በማያዳግም ሁኔታ በማረጋገጡ ለ300 ዓመት ዘብጥያ እንዲወርድ በይኖበታል፡፡

ከዚህ ከፍተኛ የካሳ ስምምነት በተጨማሪ ጾታዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴት አትሌቶች ሁሉም የአሜሪካ ብሔራዊ የጂምናስቲክና የኦሎምፒክ ኮሚቴ የቦርድ አባል መቀመጫን በቋሚነት እንዲይዙ ይደረጋል፡፡

ዶ/ር ላሪ ናስርን ለመጀመርያ ጊዜ ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባት ደፍራ ወደ አደባባይ በመውጣት ያጋለጠችው ሴት ሬችል ዴንሆላንደር ይህን የካሳ ዜና በበጎ ተቀብላዋለች፡፡

ይህ ዜና ከተሰማ በኋላ በትዊተር ሰሌዳዋ፣ ‹‹ይህ ምዕራፍ እነሆ በመጨረሻ ተዘጋ› የሚል ሐሳብ አስፍራለች፡፡

ሆኖም ግን ጉዳዩ አደባባይ ከወጣ በኋላ ለዶ/ር ላሪ ሽፋን የሰጡ የፍትሕ አካላት ከተጠያቂነት አያምልጡም ብላለች፡፡

በዶ/ር ላሪ ናስር ጾታዊ ትንኮሳ ከደረሰባቸው መካከል በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ እንደነ ሲሞን ቢለስ፣ አሊ ሬይስማን እና ማካይል ማሮኒ ይገኙበታል፡፡

ዶ/ር ናስር የብሔራዊ ቡድን ሐኪምና አሰልጣኝ ሳለ በድምሩ በ330 ሴቶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት ማድረሱን ፍርድ ቤት አረጋግጧል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከፊሉን በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ በሚያስተምርበት ጊዜ የፈጸመው ነው፡፡

ይህን ስምምነት ተከትሎ የአሜሪካ ጂምናስቲክስ ፌዴሬሽን በተፈጠረው ነገር እጅግ ማዘኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ጾታዊ ትንኮሳ ደርሶባቸው ጉዳዩን ደፍረው በአደባባይ ያወጡትን ሴቶችም ጀግኖች ናችሁ ብሏቸዋል፡፡

አሁን ከተደረሰው የካሳ ስምምነት በተጨማሪ ሚቺጋን ዩኒቨርስቲም ለተጎጂዎች 500 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ከዚህ ቀደም የተስማማ ሲሆን፣ በድምሩ የጾታ ትንኮሳ በዶ/ር ላሪ አማካኝነት ለደረሰባቸው ሴቶች የሚከፈለው የካሳ ክፍያ መጠኑ አሁን 880 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡