የዓለም ጤና ድርጅት የቻይናው ሲኖቫክ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደ

ቻይና ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዓለም ጤና ድርጅት የቻይናውን ሲኖቫክ የተባለው የኮቪድ-19 ክትባት ለአስቸኳይ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል ፍቃድ ሰጠ።

የኮሮናቫይረስ የመጀመሪያ መነሻ እንደሆነች የሚነገርላት ቻይና ያመረተችው ሲኖቫክ የተሰኘው ክትባት የአስቸኳይ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ፈቃድ ከአለም የጤና ድርጅት አገኘ።

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ውስጥ 51 በመቶው የኮሮናቫይረስ የሚያስከትላቸው የህመም ምልከቶች አልታዩባቸውም። እንዲሁም ናሙና ከተወሰደባቸው ሰዎች ውስጥ 100 በመቶ ከባድ ምልክቶችን እና ወደ ሆስፒታ ገብቶ መተኛትን መቀነስ አስችሏልም ተብሏል።

የዓለም የጤና ድርጅት ባለሙያዎች አሁንም አንዳንድ ማስረጃዎች እና የመረጃ ክፍተቶች ያለመሟላታቸውን ግን አልሸሸጉም።

ይህ ክትባት ከሲኖፋርም ቀጥሎ አረንጓዴ መብራቱን ከአለም የጤና ድርጅት የሚቀበል ሁለተኛው የቻይና ክትባት ሆኗል።

ክትባቱን ፍትሃዊ በሆነ የኮሮናቫይረስ ክትባት ማስገኛ ማዕቀፍ በሆነው የኮቫክስ ፕሮግራም ውስጥ እንዲካተት ይህ የዓለም የጤና ድርጅት ፈቃድ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

በበርካታ ሀገራት ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው ሲኖቫክ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ አዋቂዎች የሚመከር ሲሆን ከሁለት እስከ አራት ሳምንት ባለው ግዜ ውስጥ ሁለተኛው ክትባት ይሰጣል።

የአስቸኳይ ጊዜ ፈቃድ ማግኘት ማለት ክትባቱ "የደህንነት፣ የውጤታማነት እና የምርት መለኪያዎች የሆኑ ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ያሟላል" ማለት ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

በብራዚል በምትገኝ አንድ ከተማ ውስጥ በተደረገ ጥናት የሲኖቫክ ክትባት ከወሰዱ አዋቂዎች ውስጥ በኮቪድ የሚከሰት ሞት 95 በመቶ መቀነስ ችሏል።

በደቡብ ምስራቅ ብራዚላዊቷ ሳኦ ፓውሎ የምትገኘው ሴራና ከተማ 45,000 ነዋሪዎችን ይዛለች። ከእነዚህ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት የሲኖቫክ ክትባትን ከወሰዱ በኋላ የህመምተኞች ቁጥር እና ሆስፒታል የመተኛት ምጣኔ እንደቀነሰ ጥናቱ አመልክቷል ።

የዓለም የጤና ድርጅት ረዳት ዋና ዳይሬክተር ማሪያንጌላ ሲማኦ "በመላው ዓለም ያጋጠመውን ፍትሃዊ የክትባት እጦትን ለመቅረፍ በርካታ የኮቪድ ክትባቶችን ማካታት ያስፈልጋል" ብለዋል።

አምራቾች በኮቫክስ ተቋም ውስጥ እንዲሳተፉ፣ ዕውቀታቸውን እና መረጃዎቻቸውን እንዲያካፍሉ እና ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስተዋፅዖ እናደርጋለን ብለዋል።

ከሲኖቫክ ዋነኞቹ ጠቀሜታዎች አንዱ በመደበኛ ማቀዝቀዣ ውስጥ ከሁለት እስከ ስምንት ዲግሪ ሴልሺየስ ውስጥ መቀመጥ መቻሉ ነው።

ይህም በከፍተኛ ወጪ በርካታ ክትባቶችን ለማከማቸት አቅም ለሚያጥራቸው ታዳጊ አገራት ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።