የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ የውሃ እጥረት እንዲገጥመው አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ የተከሰተውን የእሳተ ገሞራ ፈንዳታን ተከትሎ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት እንዲገጥመው ማድረጉን ድንበር የለሹ የህክምና ቡድን አስታወቀ።
የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ጠቅሶ በምስራቅ ጎማ ለሚገኙ ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ገልጿል።
ግንቦት 22 በኚራጎንጎ ተራራ በተከሰተ አሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት የውሃ ማጠራቀሚያ እና ውሃ ማስተላለፊያ ቱቦወፐች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ወደ ቤታቸው መመለስ አልቻሉም።
"የተፈናቀሉ ሰዎችን አስቸኳይ ፍላጎት ለማሟላት እየሠራን ቢሆንም በቂ አይደለም" ያሉት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቡድኑ ተልዕኮ ኃላፊ የሆኑት ማጋሊ ሩዳውት ናቸው።
"ሰዎችን እንድንረዳ ሌሎች ሰብዓዊ ድርጅቶች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲሰጡን እንጠይቃለን" ብለዋል።
ድንበር የለሹ የህክምና ቡድን በአቅራቢያው በሚገኘው በሴክ ከተማ "ከ100,000 እስከ 180,000 የሚደርሱ ነዋሪዎች በአብያተ ክርስቲያናት፣ ትምህርት ቤቶች፣ መስጊዶች እና በጎዳናዎች በተጠለሉበት የህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን" አስታውቀዋል።
ከጎማ 10 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኚራጎንጎ ተራራ ከ10 ቀናት በፊት እሳተ ገሞራ በመከሰቱ የ32 ሰዎች ህይወት ማለፈፉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
በዓለም ላይ በጣም ንቁ ከሆኑት እሳተ ገሞራዎች መካከል አንዱ ከፈነዳ ጀምሮ ብዙ የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል።
የአደጋ ተጋላጭነት ባለሙያዎችን እሳተ ገሞራው ያለበትን ደረጃ ለመገምገም ድሮን (አነስተኛ ሰው አልባ አውሮፕላኖች) አሰማርተዋል።












