ግብፅ በቡድን በመድፈር የተከሰሱ ወንዶችን በነፃ ለቀቀች

ናይል ሲቲ ሆቴል

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

እአአ በ 2014 አንዲትን ወጣት ሴት በቅንጡ ሆቴል ውስጥ በቡድን ደፍረዋል በሚል የተከሰሱ ወንዶች እንዲለቀቁ የግብጽ አቃቤ ህጎች አዘዙ፡፡

የፍርድ ሂደቱ የተቋረጠው በቂ ማስረጃ ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በክስተቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ ምስክርነቶች 'ተቃርኖዎች' እንደተገኙባቸው ተናግረዋል፡፡

ክሱ የተጀመረው ባለፈው ዓመት በበይነ መረብ ይፋ የሆነው በወሲባዊ ጥቃት ለተጎዱ ሰዎች ፍትህን በሚጠይቅ የኢንስታግራም ገጽ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡

በካይሮ በሚገኘው ባለአምስት ኮከቡ ፌርሞንት ናይል ሲቲ ሆቴል ከተዘጋጀ ድግስ በኋላ ከሃብታም ቤተሰብ በተገኙ ስድስት የሚሆኑ ወንዶች አንዲት ሴትን ዕጽ በማደንዘዝ ደፍረዋል ተብሏል፡፡

ባለስልጣኖቹ ለጉዳዩ የሰጡት ቸልተኝነት ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት የሕዝብ ቁጣ ተጠናክሮ ነበር፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ስለደረሰባቸው ወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ልምዶቻቸውን በማካፈል ባለሥልጣኖቹ እርምጃ እንዲወስዱ ጫና አሳድረዋል፡፡

አቃቤ ህግ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የእስር ማዘዣ እና የጉዞ እገዳ አውጥቻለሁ ብሏል፡፡

ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ጉዳዩን ለዘጠኝ ወራት መመርመሩንም ገልጿል። ተጨማሪ ማስረጃዎች ከተገኙ ጉዳዩን በድጋሚ ሊከፍት እንደሚችል አስታውቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተጎጂዋን ጨምሮ በሆቴሉ ውስጥ የነበሩና የሌሎች 39 ሰዎችን ምስክርነት በጉዳዩ ዙሪያ ማዳመጡን ጠቁሟል፡፡