የኬንያ ፖሊስ በሰዓት እላፊ ምክንያት መንገድ በመዝጋቱ ሕክምና ያጣች ጨቅላ ሕይወቷ አለፈ ተባለ

የኬንያ ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የኬንያ ፖሊስ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ምክንያት የተጣለውን የሰዓት እላፊ ለማስከበር መንገድ መዝጋቱን ተከትሎ ሕክምና ማግኘት ያልቻለች ጨቅላ ሕይወቷ አለፈ ተባለ።

የጨቅላዋ ቤተሰብ እንደሚሉት ፖሊስ የሰዓት እላፊውን ለማስከበር በሚል የታመመች የ4 ወር ጨቅላ ይዞ ወደ ሆስፒታል የሚሄድን ታክሲ አላሳልፍም ብሏል።

የጨቅላዋ ሞት ከተሰማ በኋላ የኬንያ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ተቋም በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።

የሆነው ምን ነበር?

የአራት ወር ጨቅላ የመተንፈስ ችግር አጋጥሟት በሕምና ስትረዳ የቆየችው ጨቅላይ ተጨማሪ የሕክምና እርዳታ እንድታገኝ 'ሪፈር' ተብላ ወደ ሌላ ሆስፒታል ጉዞ መጀመራቸውን የጨቅላዋ አያት ያስረዳሉ።

ይሁን እንጂ 25 ኪ.ሜትሮችን ርቆ ወደሚገኘው እያመሩ ሳለ፤ በኮሮረናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን የሰዓት እላፊ የሚያስከብሩት ፖሊሶች አናሳልፍም እንዳሏቸው የጨቅላዋ አያት ኔሽን ለተባለው መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

"ፖሊሶቹ መንገዱን ዘግተው አናሳልፍም ባይሉ ኖሮ የልጅ ልጄ አሁንም በሕይወት ይኖር ነበር" ብለዋል የጨቅላዋ አያት።

በኬንያ ወረርሽኙን ተከትሎ ከምሽቱ አራት ሰዓት እስካ ንጋት 10 ሰዓት ድረስ ሰዓት እላፊ ተጥሏል። ከዚህ በተጨማሪም ምግብና መጠጥ ቤቶች ከምሽቱ አንድ ሰአት በኋላ አገልግሎት መስጠት አይችሉም።

ፖሊስ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም።

ባሳለፍነው ወር ደግሞ ከሰዓት እላፊው በኋላ መንገድ ላይ የነበሩ አሸከርካሪዎች እንዳያልፉ ፖሊስ መንገድ መዝጋቱን ተከትሎ በመዲናዋ ናይሮቢ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ተፈጥሮ ነበር።

በዚህ በሌሎች ምክንያቶች የኬንያ ባለስልጣናት ከፍተኛ ወቀሳ እየደረሰባቸው ቢሆንም መንግሥት ግን የሰዓት እላፊው የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰው እንደሆነ በመጥቀስ ይከራከራል።

በኬንያ እስካሁን ከ161 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 2700 ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።