ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ የኮቪድ ክትባት ለታዳጊዎች ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 ላሉ ታዳጊዎች የኮቪድ-19 ክትባት ልትሰጥ መሆኑን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስታወቁ።
እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 ላሉ ታዳጊዎች ክትባቱ በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሳቸው ይደረጋልም ተብሏል።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር 70 በመቶ ለሚሆኑ አዋቂ አሜሪካዊው እስከ ሰኔ 27 ድረስ ክትባት ለመስጠት አቅጃለሁ ብሏል።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ግብ የአሜሪካ የነጻነት ቀን በሆነው ሰኔ 27 ላይ 160 ሚሊዮን ዜጎችን መከተብን ያለመ ነው።
በየቀኑ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እየከተበች የምትገኘው አሜሪካ እስካሁን ድረስ 105 ሚሊዮን ሕዝብ የኮቪድ ክትባት ወስዷል።
ፕሬዝደንት ባይደን ባሳለፍነው ሰኞ፤ በነጻነት ቀናችን 'ከቫይረሱም ነጻ ሆነን በዓሉን እናክብረው' ሲሉ ከነጩ ቤተ-መንግሥት ሆነው ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ ከአሜሪካ የነጻነት በዓል በኋላ ሕይወት ወደ ቀደመ ሁኔታ እንዲመለስ አቅደው ሲሰሩ እንደነበረ ተናግረዋል።
ታዳጊዎችን ለመከተብ ያለው እቅድ ምንድነው?
የአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን እድሜያቸው 12 ዓመት ድረስ ለሆኑ ታዳጊዎች የፋይዘር ክትባትን ለመስጠት ሲያጤን ነበር። ባለስልጣኑ እድሜያቸው ከ16 በላይ የሆኑ ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ከዚህ ቀደም ፍቃድ ሰጥቶ ነበር።
ፕሬዝደንት ባይደን ታዳጊዎች በ15ሺህ ፋርማሲዎች ውስጥ ክትባቱን የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የፋይዘር ክትባት ለታዳጊዎች እንዲሰጥ ፍቃድ የሚሰጥ ከሆነ፤ መንግሥት እድሜያቸው ከ12 እስከ 15 ለሆኑ 17 ሚሊዮን ታዳጊዎች ክትባት ለማሰራጨት ዝግጁ መሆኑን ፕሬዝደንት ባይደን ተናግረዋል።
የፕሬዝደንቱ የጤና አማካሪ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ ሕይወት ወደ ቀደመ ሁኔታ እንዲመለስ ከተፈለገ ታዳጊ ልጆች መከተብ አለባቸው ብለዋል።
75 በመቶ የሚሆኑ አረጋውያንን በከተበችው አሜሪካ፤ በቫይረሱ የሚያዙ ታዳጊዎች ቁጥር መጨመሩ ተገልጿል።
እስራኤል ካላት ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር አንጻር በርካታ ዜጎቿን መከተብ የቻለች አገር ነች። አገሪቱ 60 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿን በመከተቧ የኮቪድ ክልከላዎችን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ አንስታለች። በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም ወደ ዜሮ እየተጠጋ ነው።












