ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፎርድ የሚያመርታቸው መኪናዎች ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሊሆኑ ነው
ግዙፉ የመኪና አምራች ፎርድ ምርቶቼ በሙሉ ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ መኪናዎች እንዲሸጋገሩ ወስኛለሁ ብሏል፡፡
ፎርድ እንዳስታወቀው ከ9 ዓመት በኋላ ሁሉም ፎርድ የሚሉ መኪናዎች የናፍጣ ወይም የቤንዚን ሳይሆኑ የኤሌክትሪክ ይሆናሉ፡፡ ይህም እንደ ፈረንጆቹ በ2030 ቢያንስ በመላው አውሮጳ እውን ይሆናል ብሏል፡፡
ከዚያ በፊት ግን በ2026 (እአአ) ሁሉም የሚሸጣቸው ተሸከርካሪዎች ወይ የኤሌክትሪክ ወይ ደግሞ ቅይጥ ይሆናሉ ብሏል፡፡
ፎርድ በዚህ ውሳኔው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበረከቱ ያሉ የነዳጅ ምርቶችን ለመቀነስ ከሚተጉ ግዙፍ ተሸከርካሪ አምራች ኩባንያዎች ጋር ተቀላቅሏል፡፡
የአውሮፓ አገራት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ከነዳጅ ምርት ጋር የተያያዙ ኩባንያዎች ላይ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡
ታላቋ ብሪታኒያ በበኩሏ የናፍጣና የቤንዚን ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ለማገድ እያውጠነጠነች ነው፡፡
ፎርድ በኮሎኝ ጀርመን የሚገኘውን ተሽከርካሪ ማምረቻ ፋብሪካ 1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ትልቁ የኤሌክትሪክ ማምረቻ ማዕከል ለማድረግ እየሰራ ነው፡፡
"ዛሬ ይፋ ያደረግነው የሽግግር እቅድ ለ90 ዓመታት አገልግሎት የሰጠው የጀርመን ኮሎኝ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመውሰድ የመጀመርያ እርምጃ ነው" ብለዋል የፎርድ ኩባንያ የአውሮጳ ፕሬዝዳንት፡፡
ሰኞ ዕለት ጃጓር ላንድሮቨር ኩባንያ ጃጉዋር የተሰኘው ምርቱ በ2025 ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ምርት እንደሚሆን ተናግሮ ነበር፡፡
ታላቋ ብሪታኒያ በነዳጅ የሚሰሩ መኪናዎችን ከ2030 በኋላ ከገበያ እንዲወጡ ለማድረግ እየሰራች ነው፡፡
በጀርመኑ ቮልስ ዋገን ኩባንያ ባለቤትነት የተያዙት ቤንትሊ ቅንጡ መኪናዎች ደግሞ በ2030 የኤሌክትሪክ መኪናዎች ይሆናሉ ብሏል፡፡
ታላቋ ብሪታኒያ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቾችን ለማበረታታትና ግዙፍ የኤሌክትሪክ መኪና ማምረቻዎች በአገሪቱ እንዲቋቋሙ ለማስቻል ግማሽ ቢሊዮን ፓውንድ መመደቧ ይታወሳል፡፡