ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጀርመን ፖሊስ ለጀሩሳሌማ ዳንስ ገንዘብ እንዲከፍል ተጠየቀ
በህዝብ ብዛት ቁጥሯ ቀዳሚ የሆነችው የጀርመሯ ኖርዝ ራይን ዌስትፋሊያ ግዛት በርካታ የፖሊስ አባላቷ ዝነኛ የሆነው የጀሩሳሌማ ዳንስ መሳተፋቸውን ተከትሎ ዋርነር ሚዩዚክ የተባለው ኩባንያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ጠይቋል።
የግዛቷ በርካታ የፖሊስ አባላት የጀሩሳሌማ ዳንስ እየደነሱ የሚያሳየው ቪዲዮ በርካታዎች አይተውታል።
በደቡብ አፍሪካዊው ማስተር ኬጂ የተዘፈነው ጄሩሳሌማ የተሰኘው ዘፈን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ጨለምተኝነት ደስታን ለመፈንጠቅ ሲባል በርካታ ሰዎች ዳንሱን በቡድን ሆኖ በመሞከር ቪዲዮዎችን ሲቀርፁ ነበር።
የዘፋኙ ዋናው ቪዲዮ በዩቲዩብ 330 ሚሊዮን ተመልካቾችን አግኝቷል።
በሮርዝ ራይን ዌስትፋሊያ ላይ የተጣለው ቅጣት በርካታ የእሳት አደጋ ሰራተኞች የቀረጿቸውን ቪዲዮዎች እንዲያጠፉ ወይም ቪዲዮ ለመስራት ያቀዱም መሰረዛቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የጀርመኑን ብሔራዊ የዜና ወኪል ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ዋርነር የሙዚቃ ኩባንያ ይህንን ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ በርካቶች በኩባንያው የፌስቡክ ገፅ ላይ ትችቶችን የሰነዘሩ ሲሆን "አሳፋሪ ባህርይ" በማለት ብዙዎች ወቅሰውታል።
የሙዚቃ ኩባንያው በበኩሉ ይህንን ድርጊቱን ትክክለኛ ነው በማለት መከራከሩን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
"በርካታ አድናቂዎች የጀሩሳሌማ አድናቂዎች በመሆናችን ደስተኛ ነን። ነገር ግን ጀርመን ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ዘፈኑን የሚጠቀሙበት ከሆነ ለዚህ ፍቃድ ያስፈልጋቸዋል፤ ገንዘብም ሊከፍሉ ይገባል" በማለት የኩባንያው ቃለ አቀባይ ለፎከስ ተናግረዋል።
"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በማንኛውም የጥበብ ዘርፍ ላሉ አርቲስቶች ተገቢው ክፍያ ሊፈፀም ይገባል። በተለይ ሌሎች የራሳቸውን ዝና ለማበልፀግ በሚጠቀሙበት ወቅት ሙዚቀኞች ከዚህ ሊከፈላቸው ይገባል" ብለዋል።