ባይደን አሜሪካ መሠረተ ልማቷን ካላሳደገች የቻይናን ተጽእኖ መቋቋም ይከብዳታል አሉ

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
ታትሟል

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ መሠረተ ልማቷን ካላሳደገች የቻይናን ተጽእኖ መቋቋም ይከብዳታል አሉ።

አሜሪካ መሰረተ ልማት ላይ የምታወጣውን ወጭ ካላሳደገች 'ቻይና ምሳችንን ቀርጥፋ ልትበላው ትችላለች' ሲሉ ፕሬዝዳንት ባይደን አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ይህንን የተናገሩት የተወሰኑ ሴናተሮችን ሰብስበው የአሜሪካ መሰረተ ልማት በሚያድግበት ሁኔታ ላይ በተወያዩበት ወቅት ነበር።

ፕሬዝዳንቱ ማስጠንቀቂያውን የተናገሩት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ያለ የስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው። በንግግራቸው ፕሬዝዳንት ዢ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ጠንካራ ሃሳብ ያነሱ ሲሆን 'መነቋቆር ለሁለታችንም አይበጀም' ማለታቸውም ተዘግቧል።

ባይደን ከአሜሪካ ሴናተሮች ጋር በነበራቸው ውይይት፤ "ሁሉን አቀፍ የሆነ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ኢንቨስት እያደረጉ ነው። በትራንስፖርት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይም ብዙ እየሰሩ ነው። ልንነቃ ይገባል" ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን።

በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ፕሬዝዳንት ባይደን በአራት ዓመት ቆይታቸው ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለአረንጓዴ የኃይል ልማት 2 ትሪሊዮን ዶላር ለማፍሰስ ቃል ገብተው ነበር።

በስፋት በታዓማኒነቱ የሚጠቀሰው አሜሪካን ሶሳይቲ ኦፍ ሲቪል ኢንጂኔርስ በ2017 (እአአ) ባወጣው መረጃ መሰረት ለአሜሪካ መሰረተ ልማት "D+" ደረጃ ሰጥቷል።

ይሄው ተቋም እንዳለው ከሆነ ታዲያ ይህንን የመሰረተ ልማት ክፍተት ለመሙላት እስከ 2025 ድረስ የ2 ትሪሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያስፈልገዋል። ነገር ግን ይህ በጀት ለመሰረተ ልማት ብቻ ሲመደብ ሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ በሁለት እጥፍ ሊጎዳ ይችላል የሚል ትንበያ አስቀምጧል።

የዓለም የኢኮኖሚክ መድረክ በ2019 አሜሪካን በመሰረተ ልማት 13ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧት ነበር። ይህም በፈረንጆቹ 2002 ከነበረችበት አምስት ደረጃዎችን አንሸራትቷታል።

በአንጻሩ ቻይና መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያከናወነች ነው። ፈጣን የባቡር ሃዲድ ግንባታ፣ ግዙፍ አፓርትመንት ግንባታ፣ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እና የሞባይል ስልክ ኔትወርክን ማስፋት እና ማዘመን ተጠቃሾች ናቸው።

"እጅግ የዘመነ የባቡር ሥራ እየሰሩ ነው፣ ከአሁን በፊት በሰዓት 225 ማይል (362.1 ኪ/ሜ) የሚፈጥን ባቡር ሰርተው አጠናቅቀዋል" በማለት ፕሬዝዳንት ባይደን ቁጭታቸውን ገልጸዋል።