ቻይና የቢቢሲ ስርጭትን አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና የቢቢሲ ዎርልድ ኒውስ ስርጭትን አገደች።
የአገሪቱ የቴሌቪዥን እና ራዲዮ ተቆታጣሪ መስሪያ ቤት ትናንት ምሽት ይፋ እንዳደረገው፤ የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ይዘቶች በቻይና እንዳይረሰራጩ ለአንድ ዓመት ታግዷል።
ቻይና ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ እና የኡጉር ሙስሊሞችን በተመለከ ቢሲሲ የሚሰራቸውን ዘገባዎች ስትተች ቆይታለች።
ቢቢሲ በበኩሉ በቻይና መንግሥት ወሳኔ 'ቅር ተሰኝቻለሁ' ብሏል።
በተመሳሳይ የዩናይትድ ኪንግደም መገናኛ ብዙሃን ተቆጣጣሪው ተቋም 'ኦፍኮም' የቻይናው ዓለማ አቀፍ የቴሌቪዥን ኔትወርክ (ሲጂቲኤን) በዩናይትድ ኪንግደም ያለውን የስርጭት ፈቃድ መንጠቁ የሚታወስ ነው።
ኦፍኮም ከዚህ ውሳኔ የደረሰው በያዝነው ወር መጀመሪያ የሲጂቲኤን የስርጭት ፈቃድ 'ስታር ቻይና ሚዲያ ሊሚትድ' በተባለ ሌላ ተቋም ጥቅም ላይ ሲውል በማግኘቴ ነው ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ሲጂቲኤን የብሪቲሽ የመገናኛ ብዙሃን የስርጭት መመሪያን በመተላላፍ ባሳለፍነው ዓመት የዩኬ ዜግነት ያለው ፒተር ሃምፕሬይ ተገድዶ ቃሉን የሰጠበትን ሂደት አሰራጭቷል የሚል ክስም ቀርቦበት ነበር።
የቻይና የአገር ውስጥ ፊልም፣ ቲቪ እና ሬድዮ አስተዳደር የቢቢሲ ዎርልድ ኒውስ ስለ ቻይና የሚሰራቸው ዘገባዎች 'በከፍተኛ ሁኔታ' የስርጭት መመሪያዎችን የሚጥስ ነው፤ እና ዘገባዎቹ 'ተዓማኒነት የሌላቸው' ናቸው ብሏል።
አክሎም ቢቢሲ የቻይናን ብሄራዊ ጥቅሞች ጎድቷል ሲል ምክንያቱን አስቀምጧል።
በዚህም ምክንያት ቢቢሲ ዎርልድ ኒውስ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለማሰራጨት የጠየቀው ፈቃድ ተቀባይነት አይኖረውም ብሏል።
ይህን ተከትሎ ቢቢሲ ባወጣው መግለጫ '' የቻይና ኃላፊዎች ይህን መሰል እርምጃ ለመውሰድ በመወሰናቸው አዝነናል። ቢቢሲ በዓለም ዙሪያ ታማኝ የሆነ የሚዲያ ተቋም ነው። ከመላው ዓለም የተወጣጡ ዜናዎችን ያለምንም ፍርሀት፣ መድልዎ እና በሚዛናዊነት የሚዘግብ ተቋም ነው'' ብሏል።
የቢቢሲ ዓለማ አቀፍ አገልግሎት በመላው ዓለም በእንግሊዝኛ የሚሰራጭ ሲሆን በቻይና ደግሞ ስርጭት በእጅጉ የተወሰነ ነው። የቢቢሲ ስርጭት የሚታየው በአንዳንድ ዓለማ አቀፍ ሆቴሎችና ዲፕሎማቲክ ግቢዎች ውስጥ ብቻ ነው። ይህ ማለት ደግሞ አብዛኛዎቹ ቻይናውያን ስርጭቱን ማየት አይችሉም።
የውጭ ጉዳይ ጸሃፊው ዶሚኒክ ራብ የቻይናን ውሳኔ ''ተቀባይነት የሌለው የመገናኛ ብዙሀንን ነጻነት የሚጋፋ'' በማለት ገልጸውታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በበኩሉ በይፋዊ የትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት የቻይናን ውሳኔ ያወገዘ ሲሆን፤ ቻይና መገናኛ ብዙሃንን ለማፈን የምታደርገው ጥረት አካል ነው በማለት ወቅሷል።
የቻይና እና የዩኬ ግንኙነት በቅርብ ወራት ውስጥ እየሻከረ መጥቷል። ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የሆንግ ኮንግ ጉዳይ ነው።
ዩኬ ለ5.4 ሚሊየን የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ወደ ዩኬ መጥተው የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት የሚያስችላቸውን ቪዛ ማስተዋወቋ ቻይና አስቆጥቶ ነበር።
በተጨማሪም ባለፉት ሁለት ዓመታት ቻይና በተለያዩ ምክንያቶች የውጭ አገራት መገናኛ ብዘሃንን እያገደች ትገኛለች። በያዝነው ዓመት ብቻ እንኳን ለተለያዩ ሶስት የአሜሪካ ጋዜጣዎች የሚሰሩ ጋዜጠኞች ተባረዋል።
የቢቢሲ ድረ-ገጽም ሆነ መተግበሪያ በመላው ቻይና አይሰራም።












