በታንዛኒያ አዲስ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ተከሰተ

ታትሟል

ምንነቱ በውል ያልታወቀ በሽታ በታንዛኒያ ደብቡ ምዕራብ አካባቢ መከሰቱን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአካባቢው የጤና ሃላፊዎች እንዳረጋግጡት በዚሁ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ ምክንያት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል። አማሟታቸውም በበሽታው በተያዙ በሰዓታት ውስጥ መሆኑ ነው የተነገረው።

ከሚታመሙት ሰዎች ብዙዎቹ ወንዶች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በሽታው ከጉበት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

የአገሪቱ የጤና ሚንስቴር ወደ ስፍራው አጥኝ ቡድን የላከ ቢሆንም ስለ ክስተቱ ግን ያለው ነገር የለም።

የአካባቢው የጤና ሃላፊ ስለ በሽታው መረጃ ከሰጠ በኋላ የታንዛንያ የጤና ሚንስቴር ከስራው አግዶታል።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ይህ አይነት በሽታ አዲስ ያልሆነ እና ምልክቶቹም ከፈረንጆቹ 2018 ቀደም ብለው የተስተዋሉ መሆናቸውን ገልጿል።

ሚንስቴሩ ወደፊት በቂ ጥናት በማድረግ ሙሉ መረጃ ለማጋራት ቃል የገባ ሲሆን ሕዝቡ እንዲረጋጋም ጥሪ አቅርቧል።

ታንዛንያዉያን የኮሮናቫይረስ በሽታን ለመቋቋም የሚያስችሉ ነገሮችን ማድረግ እንዳለባቸው ቀደም ሲል መናገራቸው ይታወሳል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ ደግሞ "ጸሎታችሁ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል" በማለት ታንዛኒያ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆኗን አውጀው ነበር።

የጤና ሚንስቴሩም በቀጣይ ለኮሮናቫይረስ የሚሆን ክትባት ወደ አገር ቤት ለማስገባት እቅድ እንደሌለው ገልጿል።