ደቡብ አፍሪካ የአስትራዜኔካ ክትባት ይቆየኝ አለች

ታትሟል

ደቡብ አፍሪካ በቀጣይ ሳምንት አስትራዜኔካ ሰራሽ የኮቪድ ክትባት ለዜጎቿ ለመስጠት የያዘችውን ሃሳብ ሰረዘች።

ደቡብ አፍሪካ ከዚህ ውሳኔ የደረሰችው የአስትራዜኔካ ክትባት በአገሪቱ የተከሰተውን አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መከላከለያ ላይ አመርቂ ውጤት ባለማሳየቱ ነው።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ 90 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች እየተያዙ ያሉት በአዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ነው።

2ሺህ ሰዎችን ያሳተፈው ምርምር ውጤት መካከለኛ እና ዝቅተኛ ምልክት በሚታይባቸው ሰዎች ላይ ክትባቱ በጣም አናሳ የመከላከል አቅም እንዳለው ያሳያል ተብሏል።

ደቡብ አፍሪካ 1 ሚሊዮን የአስትራዜኔካ ክትባት የተቀበለች ሲሆን በቀጣይ ሳምንት ክትባቱን ለዜጎቿ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነበረች።

ትናንት የደቡብ አፍሪካ የጤና ሚንስትር አሁን የተገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ ክትባቱን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ተጨማሪ ምክረ ሃሳብ እስኪመጣ ድረስ ለጊዜው ክትባቱ እንዲቆይ መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል።

እስከዚያው ግን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፋይዘር ክትባትን ሌዘጎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ማቅረብ እንደሚጀምር ሚንስትሩ ገልጸዋል።

ምርምሩ የተካሄደው በደቡብ አፍሪካ ዊትወተርስራንድ በዩኒቨርሲቲ ሲሆን የምርምሩ ሂደት ግን በሌሎች አልፈተሸም።

ምርምሩን የመሩት ፕሮፌሰር ሻቢር ማዲ "እንደ አለመታደል ሆኖ የአስትራዜኔካ ክትባት ቀላል እና መካከለኛ ህመም ባለባቸው ሰዎች ላይ አልሰራም" ብለዋል።

ይሁንና ጥናቱ ያተኮረው በአማካይ ዕድሜያቸው 31 ዓመት የሆኑ ሰዎች ላይ በመሆኑ ክትባቱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት የማሕበረሰብ ክፍሎች ወይም በዕድሜ የገፉ እና ተጓዳኝ በሽታ ያላቸው ሰዎች ላይ የሚያመጣው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል ጥናት አለማድረጋቸውን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የኦክስፎርዱን የአስትራዜኒካ ክትባት ምርምር በበላይነት የመሩት ፕሮፌሰር ሳራህ ጂልቤርት ክትባቶች አንድ ብቻ ሳይሆን በዛ ያሉ በሽታዎችን ይከላከላሉ ብለዋል።

አጥኝዋ እንደሚሉት ምናልባትም ለእንደ ደቡብ አፍሪካው አይነት ኮሮናቫይረስ ውጤታማ የሚሆን 501.ቪ2 ወይም ቢ.1.351 የተሰኙ ማሻሻያ የተደረገባቸው ክትባቶች በአቅራቢዎች በኩል በዚህ ዓመት መጨረሻ ሊቀርቡ ይችላሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት አዳዲስ የቫይረስ አይነቶች ሲከሰቱ ለተከሰቱት ቫይረሶች የሚሆኑ ማሻሻያ የተደረገባቸው ክትባቶችን ለማቅረብ ሳምንታት ወይም ወራት ሊወስድ ይችላል።

እስካሁን የተደረጉ የመጀመሪያ ሙከራዎች እንደሚያሳዩት ሞደርና የተሰኘው ክትባት ደቡብ አፍሪካ ለተፈጠረው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ውጤታማ ሲሆን ዩናትትድ ኪንግደም ውስጥ ለተገኘው አዲስ የቫይረሱ ዝርያ ደግሞ የአስትራዜኔካ ፍቱን ነው ተብሏል።