በዲሞክራቲክ ኮንጎ አንዲት ሴት በኢቦላ በሽታ ሕይወቷ አለፈ

ታትሟል

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ በኢቦላ በሽታ የሰው ሕይወት ማለፉን የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር አስታወቀ።

በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ቡቴምቦ በምትሰኝ ከተማ ነዋሪ የነበረች ሴት በኢቦላ በሽታ ከተያዘች በኋላ ሕይወቷ ማለፉ ተገልጿል።

ቡቴምቦ ከዚህ ከቀደም የኢቦላ በሽታ ተቀስቅሶ በርካቶች ሕይወታቸውን ያጡባት ከተማ ነች። በኢቦላ በሽታ ሕይወቷ ያለፈው ይህች ሴት ከዚህ ቀደም በበሽታው ተይዞ ያገገመ ሰው ባለቤት ነች ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው ሕይወቷን ካጣችው ሴት ላይ የተወሰደው ናሙና በኢቦላ በሽታ መያዟን አረጋግጧል ብሏል። የኢቦላ በሽታ ምልክትም ይታይባት ነበር ተብሏል።

የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የጤና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥፍራው መላኩን አስታውቋል። የዓለም ጤና ድርጅትም ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ በአከባቢው ያለው የደህንነት ስጋት የበሽታ መቆጣጠሩ ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ለ10ኛ ጊዜ ተቀስቅስቅሶ የነበረው እና ለሁለት ዓመታት በዘለቀው የኢቦላ ወረርሽኝ 3481 ሰዎች በበሽታው ተይዘው 2299 ሰዎች ሞተዋል።

በአገሪቱ የኢቦላ በሽታ ሲመዘገብ ይህ ለ12ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በበሽታው የተያዘ ሰው የተገኘው ከወራት በፊት በምዕራባዊ የአገሪቱ ክፍል ነበር።

የኢቦላ በሽታ ምንድነው?

ኢቦላ ቫይረስ ሲሆን ድንገተኛ እና አደገኛ የሆነ ትኩሳት፣ ድካም፣ የጡንቻ እና የጉሮሮ ሕመም ያስከትላል።

በሽታው እየጠና ሲሄድ ትውከት፣ ተቅማጥ ይጀምራል። ባስ ሲል ውስጥ እና ወደ ውጪ መድማትን ያስከትላል።

በበሽታው የሚያዙ ሰዎች በድርቀት እና የሰውነት አካላት መስራት ማቆም ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በኢቦላ የሚያዝ ሰው በበሽታው የመሞቱ እድል 50 በመቶ ነው ይላል።

አንድ ሰው በኢቦላ በሽታ ሊያዝ የሚችለው በኢቦላ በሽታ የተያዘ ሰው ደም፣ ትውከት፣ ሰገራ እና ፈሳሽ ወደ አፍና አፍንጫ አልያም ቁስለት ያለበት ቆዳ ላይ ካረፈ ነው።