ኮሮናቫይረስ ፡ በቫይረሱ የተያዙ በመጀመሪያዎቹ ቀናት የማስተላለፍ እድላቸው ሰፊ መሆኑ ተጠቆመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ምልክቶች በማያሳዩባቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት ውስጥ ቫይረሱን የማስተላለፍ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን አንድ ጥናት ጠቆመ፡፡
እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች ከሆነ ቫይረሱ ያለባቸውን ቀደም ብሎ በለይቶ ማቆያ ማስገባት ስርጭቱን ለማስቆም ወሳኝ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የጥናት ውጤቱ በላንሴት ማይክሮብ ላይ ታትሟል።
ግለሰቦች የማስተላለፍ ዕድላቸው በብዙ ነገሮች ላይ የተመረኮዘ ሲሆን ራሱን የሚያባዛ ቫይረስ እና በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን ስርጭቱን ከሚወስኑት መካከል ናቸው።
አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሰዎች የበሽታ ምልክቶች ከማሳየታቸው በፊት እና በቫይረሱ በተያዙ የመጀመሪያው ሳምንት በጣም አስተላላፊ ናቸው፡፡
በሆስፒታል ውስጥ የበሽታው ምልክት ያለባቸውንና ቫይረሱ የተገኘባቸውን ጨምሮ ሳይንቲስቶች በኮቪድ-19 ላይ 79 ዓለም አቀፍ ጥናቶችን መርምረዋል።
ተመራማሪዎች ኢንፌክሽኑ ከጀመረ እስከ ዘጠኝ ቀናት ድረስ ከተወሰዱ የጉሮሮ ናሙናዎች ውስጥ ዋነኛ ቫይረሶችን መለየት እና ማባዛት ችለዋል፡፡
ምልክቶቹ በጀመሩበት ጊዜ ወይም በአምስት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ የቫይረስ ስርጭት እንደሚኖር ከሰዎች የጉሮሮ ናሙና ማወቅ ችለዋል።
ምልክቶቹ ከጀመሩ በአማካይ እስከ 17 ቀናት በአፍንጫ እና በጉሮሮ ናሙናዎች ንቁ ያልሆኑ የቫይረስ ቁርጥራጮች ተገኝተዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ እነዚህ ቁርጥራጮቻቸው ከዘጠኝ ቀናት በላይ ቢቀጥሉም አብዛኛዎቹ ሰዎች የማስተላለፍ ዕድላቸው አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡
የሴንት አንድሪውስ ዩኒቨርስቲ ባልደረባው ዶ/ር ሙጌ ሴቪክ ለቢቢሲ እንደገለጹት ግኝቶቹ ሰዎች ገና በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በጣም አስተላላፊ እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡
"ሰዎች የሕመም ምልክቶችን እንዳሳዩ እንዲለዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምርመራ ውጤቶችን በሚያገኙበት ጊዜ በጣም አስተላላፊ የሚሆኑበትን ደረጃቸውን ያልፉ ይሆናል።"
"ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ወዲያውኑ ራሳቸውን ያለዩበትን ምክንያት በመመልከት ይህንን እንዲያደርጉ ልንረዳቸው ይገባል" ብለዋል፡፡
ጥናቱ ምልክት የማያሳዩ ሰዎችን አላካተትም። ሆኖም ሌሎች ጥናቶችን እንደሚያስጠነቅቁት ሰዎች የበሽታ ምልክቶች ከማሳየታቸው በፊትም አስተላላፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና ምንም ዓይነት የበሽታ ምልክት ሳይኖር ቫይረሱ ሊተላለፍ ይችላል፡፡
የእንግሊዝ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ካላቸው ወዲያውኑ ራሳቸውን ቢያንስ ለ 10 ቀናት ማግለል አለባቸው፡፡












