በቶክዮ ኦሎምፒክስ ታዳሚዎች ሊገኙ ይችላሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክስ ኮሚቴ ኃላፊ ቶማስ ባህ፤ በቶክዮ ኦሎምፒክስ ላይ ታዳሚዎች እንደሚገኙ "በጣም እርግጠኛ ነኝ" አሉ።
ታዳሚዎች ወደ ቶክዮ ከመሄዳቸው በፊት እንዲከተቡ ለማስቻል ኮሚቴው ጥረት እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
አሁን ጃፓን ሄደው ስለ ኦሎምፒክስ ውድድር ውይይት እያደረጉ ነው።
ዘንድሮ ሐምሌ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ኦሎምፒክስ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ተራዝሟል።
በጎርጎሮሳውያኑ 2021 ሐምሌ ላይ ከ200 አገሮች የተውጣጡ 11,000 ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዮሺሂንዴ ሱጋ ጋር የተነጋገሩት የኦሎምፒክስ ኮሚቴ ኃላፊው ለኤኤፍፒ "በኦሎምፒክስ ስቴድየም ታዳሚዎች እንደምናስተናግድ በጣም እርግጠኛ ነን" ብለዋል።
ከዓለም አቀፉ የኦሎምፒክስ ኮሚቴ ባሻገር ጃፓንም ውድድሩ እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ሰጥታለች።
የጃፓን ቶክዮ ኦሎምፒክስ 2020 ዋና ኃላፊ ቶሺሮ ሙቶ፤ ዓመቱ መባቻ ላይ አንዳንድ ውድድሮች በአነስተኛ ታዳሚዎች እንደሚካሄዱና አገራት የሚመድቧቸው የቡድን አባላት ሊቀነሱ እንደሚችሉም ተናግረው ነበር።
የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክስ ኮሚቴ ኃላፊ ቶማስ ባህ ባለፈው ሳምንት አንዳንድ ተወዳዳሪዎች ውድድሩን ሰርዘው እንደሆነ ተጠይቀው፤ ማንም ውድድሩን እንዳልሰረዘ አስረግጠው ምላሽ ሰጥተዋል።
ምክትላቸው ደግሞ "ኮቪድ-19 ቢኖርም ባይኖርም ውድድሮቹ ይካሄዳሉ" ብለዋል።
የኦሎምፒክስ ሚንስትር ሴኮ ሃሺማቶ ውድድሩ "በዚህም አለ በዛ ይካሄዳል" ሲሉ ተናግረዋል።
እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ለወረርሽኙ ክትባት ሊመረት እንደሚችል የሚጠቁሙ ዜናዎች እየተሰሙ ነው።












