ሩሲያ ከሁሉም ስፖርታዊ ውድድሮች ልትታገድ ትችላለች

የሩሲያ አትሌት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዓለማ አቀፉ የጸረ አበረታች መድሃኒቶች ኤጀንሲ (ዋዳ) ከሩሲያ ላቦራቶሪዎች የተገኙት መረጃዎች ወጥ ስላልሆኑ ሃገሪቱ ከማንኛውም ስፖርታዊ ውድድሮች ልትታገድ ትችለች ብሏል።

ሩሲያ ጉዳዩን በአግባቡ ለማስረዳት ሶስት ሳምንታት የተሰጣት ሲሆን አጥጋቢ ምላሽ የማትሰጥ ከሆነ ግን ከኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒየንሺፕ ውድድሮች መታገዷ እንደማይቀር ኤጀንሲው አስታውቋል።

በተጨማሪም ማንኛውም አይነት ውድድሮች ከማዘጋጀትም ልትታደግ እንደምትችል አስጠንቅቋል።

''ከላቦራቶሪ ውጤቶቹ መካከል ብዙዎቹ መጥፋታቸውን አረጋግጠናል'' ሲሉ ጆናታን ታይለር የተባሉ የዓለማ አቀፉ የጸረ አበረታች መድሃኒቶች ኤጀንሲ ከፍተኛ ሃላፊ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ሩሲያ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባት ለሶስት ዓመታት የተጣለባትን እገዳ ከጨረሰች በኋላ ነበር ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ የላቦራቶሪ ውጤቶቹን ለዋዳ ያስረከበችው።

የዋዳ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሰኞ ዕለት እንዳስታወቁት መረጃዎቹ ወጥነት ስለሚጎድላቸውን ሆን ተብሎ የጠፉም ስላሉ ይፋዊ የሆነ ምርመራ ተጀምሯል።

ሩሲያ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች ከሁሉም ስፖርታዊ ውድድሮች ልትታገድ የምትችል ሲሆን ቅሬታ ካላት ደግሞ ለዓለማ አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት እንደምትችል ኮሚቴው ገልጿል።

የዓለማ አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በዋዳ ቀርቦለት የነበረውን ሩሲያን ከ2016ቱ የሪዮ ኦሎምፒክ የማገድ ሃሳብ ወደጎን ብሎት የነበረ ሲሆን በ2018 በፒዮንግያንግ በተካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ግን ሩሲያ እንዳትሳተፍ ማድረጉ ይታወሳል።

የዓለማ አቀፉ አትሌቲክስ ሻምፒየንሺፕ ከአራት ቀናት በኋላ በኳታር ዶሃ የሚጀመር ሲሆን የሩሲያ ተሳታፊዎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አልታወቀም።

''ወጣም ወረደ ሩሲያ ለመደበቅ የሞከረቸው መረጃ ካለ በቀጣዩ ዓመት በቶክዮ ከሚዘጋጀው የቶክዮ ኦሎምፒክና ከ2022 ዓለም ዋንጫ መታገዷ አይቀርም'' ብለዋል ጆናታን ታይለር።

የሩሲያው ስፖርት ሚኒስትር ፓቬል ኮሎብኮቭ ''ምን አይነት የመረጃ መለያየት እንደተፈጠረ ሊነግሩን ይገባል፤ ልዩነቶቹ ከምን ጋር የተያያዙ መሆናቸውም ግልጽ መደረግ አለበት'' ማለታቸውን 'ታስ' የተባለው የዜና ወኪል ዘግቧል።

''የዲጂታል ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ከሁለቱም በኩል በትብብር እየሰሩ ነው። በእኛ በኩል ማንኛውም አይነት ትብብርና እርዳታ ለማድረግ ዝግጁ ነን'' ብለዋል።

ሩሲያ ባለፈው ዓመት የላቦራቶሪ ውጤቶቹን ለዋዳ ስታስረክብ የተቀመጠላትን ቀነ ገደብ አሳልፋ ነበር። ይህ ደግሞ ብዙ ጥርጣሬዎች እንዲፈጠሩ አድርጎ ነበር።