በሊቢያ የአንድነት መንግሥት ለመመስረት ንግግር ሊጀመር ነው

ሰባ አምስት ሰዎች በድርድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በሊቢያ ነፍጥ አንስተው ለረዘዝም አመታት ሲፋለሙ የነበሩ ተዋጊዎች የአገሪቱን ግጭት ተነጋግሮ ለመፍታትና የአንድነት መንግሥት መመስረት በሚያስችላቸው ነጥቦች ላይ ለመወያየት በቱኒዚያ ይገናኛሉ።

ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገውና በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት እና የአገሪቱን ምስራቃዊ ክፍል ተቆጣጥሮ የሚገኘው የጄነራል ካሊፍ ኻፍታር ጦር ናቸው።

ሁለቱ ወገኖች የአንድነት መንግሥት ስለ መመስረት እና ምርጫ ስለሚካሄድበት ሁኔታ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሁን ፊት ለፊት ለመገናኘት ከመወሰናቸው በፊት ባለፍ ወር በቨርቹዋል ስብሰባ ሲያደርጉ ነበር ተብሏል።

ባለፈው ወር በጄኔቫ ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግም ተፈራርመዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የተመረጡና የሊቢያን ፖለቲካ፣ ወታደራዊ እና ማህበራዊ ሕይወት የሚወክሉ ሰባ አምስት ሰዎች በድርድሩ ላይ እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።

እንደ ፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉታሬስ " ይህንን አሳዛኝ ግጭት ለማቆም እድሉ አላችሁ። የአገራችሁን የወደፊት እድል ለመቅረጽ ጊዜያችሁ አሁን ነው" ብለዋል።

ይህ በተባበሩት መንግሥታት የተጠራውና ሊቢያውያን የሚያደርጉት ይህ ውይይት አገሪቱ ወደፊት የምትመራበት የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ እና የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የተባበሩት መንግሥታት በሊቢያ ያለው ልዑክ ተጠባባቂ ኃላፊ ስቴፈን ዊሊያምስ ይህንን ስብሰባ "ልዩ እድል" ሲሉ ጠርተውታል። አክለውም ተሰብሳቢዎቹ ለአገራቸው ሲሉ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተማጽነዋል።

ሊቢያ በአገሯ ውስጥ በሚካሄደው የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተቀናቃኞች መካከል በሚካሄደው ግኝት የተነሳ ከፍተኛ ውድመትን አስተናገግዳለች።

አገሪቷ ወደ መረጋጋት ለመመለስ በወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ኃይሎች መካከል ረዥም ጊዜ የሚዘልቅ መረጋጋትና ሰላም ሊኖር ይገባል ሲሉ የሊቢያን ቀውስ የሚከታተሉ ሰዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።