ሊቢያ ፡ የሊቢያ ተፋላሚ ኃይሎች ለንግግር በሞሮኮ ተቀምጠዋል

የሊቢያ ኃይሎች በውይይት ላይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ሁለቱ የሊቢያ ተዋጊ ኃይሎች በሞሮኮ ለንግግር ተቀምጠዋል።

ሊቢያ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ አምባገነኑ ሙአመር ጋዳፊ በሕዝባዊ አመጽ ከመንበራቸው ተወግደው ከተገደሉ በኋላ ከመረጋጋት ርቋት በጦርነት እየታመሰች ትገኛለች።

በሊቢያው ጦርነት የበላይነትን ለመያዝ የሚፋለሙት ዋነኞቹ ኃይሎች ከሁለት ሳምንታት በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ነበር።

ሊቢያ ሁለት መንግሥት ሥር የወደቀች ሲሆን አንዱ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያገኘው በጠቅላይ ሚንስትር ፋዬዝ አል-ሴራጅ የሚመራውና መቀመጫውን ትሪፖሊ ያደረገው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አብዛኛውን የአገሪቱን ከተሞች የሚቆጣጠረውና በምሥራቃዊዋ ቱብሩክና ቤንጋዚ ከተሞች መቀመጫውን ያደረገው የጦር አዛዡ ጄኔራል ኻሊፋ ሃፍታር የሚመሩት ነው።

የሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቦሪታ በመክፈቻው ላይ እንደተናገሩት ሞሮኮ ይህንን ድርድር ስታሰተናዳ አንድም አጀንዳ ደብቃ አይደለም። ሊቢያውያን ልዩነቶቻቸውን ተነጋግረው እንዲፈቱ ለማስቻል ሌላ እድል ለመስጠት እንጂ ብለዋል።

አሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የሰጠው መንግሥት በፈረንጆቹ በ2015 የተመሰረተው በሞሮኮ እንደነበር አይዘነጋም።

ጀነራል ሃፍታር "እስላማዊ አሸባሪዎችን" እዋጋለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስና ዮርዳኖስ ጽንፈኞች ከቀጠናው መጽዳት አለባቸው በማለት አጋርነታቸውን ከጀነራሉ ጋር አድርገዋል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በሩሲያ መንግሥት ተከፋይ የሆኑ የሌሎች አገራት ቅጥረኛ ወታደሮች ከጀነራሉ ጎን ሆነው ይዋጉ ነበር። የክሬምሊን መንግሥት ግን ቀጥተኛ ተሳትፎ የለኝም ብሏል።

በሌላኛው በኩል ደግሞ ቱርክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና የያለውን መንግሥት ትደግፋለች። ከመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ውሰጥ ተገልላ የምትገኘው ኳታር፤ በሊቢያ ጉዳይ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከቱርክ ጎን ተሰልፋለች።