የ12 ዓመቱ ታዳጊ 69 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረ የ'ዳይኖሰር' ቅሪተ አካል አገኘ

የፎቶው ባለመብት, Nature Conservancy of Canada
ካናዳ፣ አልበርታ ውስጥ ከአባቱ ጋር በተራራማ አካባቢ እየተጓዘ የነበረ የ12 ዓመት ታዳጊ፤ 69 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረ የ'ዳይኖሰር' ቅሪተ አካል አግኝቷል።
ታዳጊው ናታን ህሩሽኪን ሐምሌ ላይ ቅሪተ አካል በሚበዛበት አካባቢ እየተጓዘ ሳለ አለት ስር ቅሪተ አካሉን ተመልክቷል።
በወቅቱ ዐይኑን ማመን እንዳልቻለ "ምን እንደምናገር ጠፋኝ" ሲል ገልጿል።
ታዳጊው ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ "መደሰት እንዳለብኝ ባውቅም በወቅቱ የዳይኖሰር ቅሪተ አካል በማግኘቴ በጣም ከመደንገጤ የተነሳ ልደሰት ሁሉ አልቻልኩም" ብሏል።
ናታን ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ ስለ ዳይኖሰሮች የማወቅ ጉጉት አለው። የካናዳ የተፈጥሮ ጥብቅ ቦታ አካባቢ መጓጓዝም ያዘወትራል።
"አጥንታቸው እንደኛ ካለ አጥንት ተነስቶ እንዴት የአለት ያህል ጠንካራ እንደሚሆን ሳስብ እጅግ እገረማለሁ" ይላል።
ከዓመት በፊት የተሰባበሩ ቅሪተ አካሎች ሲያገኙ፤ አባትየው ከአለት የወደቁ እንደሆኑ ገምቶ ነበር።
ናታን ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ለማጣራት ወስኖ ዘንድሮው ወደተራራማ አካባቢው ተመለሱ።
ቅሪተ አካሎች ከአንድ ኮረብታ ጥግ ሲያዩ ናታን "አባዬ እዛ ላይ መውጣት አለብህ" አለው።
አባትየው ዲዮን ህሩሽኪንም ልጁ አንዳች ነገር ማግኘቱን ተረዳ።
"ከድንጋይ የተሠራ ቅሪተ አካል ይመስላል። ጭን አካባቢ የሚገኝ አጥንትም ይመስል ነበር" ሲል ይገልጻል።
ቅሪተ አካሉ ጥብቅ ቦታ ስለሚገኝ የሕግ ከለላ እንዳለው የሚያውቀው ናታን፤ ሮያል ቲረል ሙዝየም ድረ ገጽ ላይ ስለ ቅድመ ታሪክ ሕይወት ያጠና ጀመር።

የፎቶው ባለመብት, Nature Conservancy of Canada
ከዛም ሙዝየሙ የቅሪተ አካሉን ፎቶና የተገኘበትን ትክክለኛ ቦታ እንዲያሳውቁ አባትና ልጅን ጠየቀ። እነሱም መረጃውን ሰጡ።
ባድላንድስ ተብሎ የሚታወቀው ተራራማ አካባቢ በርካታ ቅሪተ አካሎች ይገኛሉ። እአአ በ1980ዎቹ ጆሴፍ ታይረል ያገኛቸው የዳይኖሰር ቅሪተ አካሎች፤ 'አልበርቶሳረስ' የሚል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ሆኖም ግን ናታን እና አባቱ ይጓዙበት የነበረው መንገድ ላይ ቅሪተ አካል ተገኝቶ ስለማያውቅ፤ ሙዝየሙ ባለሙያዎችን ወደስፍራው ልኳል።
ባለሙያዎቹ እስካሁን ከ30 እስከ 50 የሚደርስ ቅሪተ አካል አግኝተዋል። ቅሪተ አካሉ ሀድሮሶር የተባለና ከሦስት እስከ አራት ዓመት ገደማ እንደሆነው የሚገመት ዳይኖሰር ነው።
ናታን "እንደማንኛውም ልጅ ነበርኩ። የምወደውም ታይኖሰረስ ሬክስን ነበር። ቅሪተ አካሉን ካገኘሁ በኋላ ግን ሀድሮሶርን መውደድ ጀምሬያለሁ" ብሏል።
ሙዝየሙ እንዳለው፤ ቅሪተ አካሉ 69 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያለው ስለሆነ፤ ዳይኖሰሩ በሳይንስ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል።
በተመሳሳይ ዘመን ላይ የነበሩ ቅሪተ አካሎች እስካሁን እምብዛም አልተገኙም።
የሙዝየሙ የፓሌዎአርኪዮሎጂ ሰብሳቢ ፍራንኮስ ቴይረን "የዚህ ወጣት ሀይድሮሶር ቅሪተ አካል ግኝት ትልቅ ዋጋ አለው። ጥቂት መረጃ ብቻ ያለን ጥንታዊ ዘመን ላይ የተሻለ ግንዛቤ ይፈጥራል። አልበርታ ውስጥ ምን አይነት ዳይኖሰሮች ወይም እንስሳት እንደኖሩ ያሳየናል" ብለዋል።
የአባትና ልጅ ግኝት በዳይኖሰር ዝግመተ ለውጥ የነበረውን የእውቀት ክፍተት እንደሚሞላም አስረድተዋል።












