ቴት ሞደርን፡ ከ30 ሜትር ከፍታ ላይ የተወረወረው ታዳጊ ያለ ድጋፍ መቆም ቻለ

ታትሟል

ታዳጊው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ያመራው ከቤተሰቦቹ ጋር ለንደንን ለመጎብኘት ነበር።

በጉብኝታቸው ግን ያላሰቡት ነገር ነበር የገጠማቸው። በለንደን የሚገኘውን የአርት ጋለሪ በሚጎበኙበት ወቅት ነበር አንድ ወጣት የ6 ዓመቱን ታዳጊ 30 ሜትር ከፍታ ላይ ከሚገኝ በረንዳ ላይ አንስቶ የወረወረው።

ታዳጊው በወቅቱ ከፍተኛ ጉዳት ነበር ያጋጠመው። በሕይወት ይተርፋልም ያለ አልነበረም።

አሁን ግን በጎ ዜና ተሰምቷል።

ይሄው በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ከሚገኘው ቴት ሞደርን በረንዳ ላይ የተወረወረው ታዳጊ፤ ያለ ድጋፍ መቆም መቻሉን ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል።

ታዳጊው ባሳለፍነው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከ30 ሜትር ከፍታ ላይ ከሚገኝ በረንዳ ላይ ሲወረወር እድሜው 6 ነበር።

ታዳጊውን የወረወረው የ18 ዓመት ወጣት ጆንቲይ ብሬቨርይ በግድያ ሙከራ ተከሶ 15 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ ባሳለፍው ሰኔ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ፍርዱ ሲተላለፍ ፍርድ ቤቱ ታዳጊው እስከ ጎርጎሮሳዊያኑ 2022 ድረስ ጥብቅ ክትትል ሊያስፈልገው እንደሚችል የቀረበለትን ማስረጃ ሰምቶ ነበር።

ታዳጊው የአንጎል ደም መፍሰስ፣ የአከርካሪ አጥንት መሰንጠቅ ያጋጠመው ሲሆን ዊልቸር ለመጠቀም ዳርጎታል።

ስሙ ያልተገለፀው ታዳጊው ፈረንሳይ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል ከመሄዱ በፊት በሮያል ለንደን ሆስፒታል ሕክምና ሲከታተል ነበር።

ጥቃቱ ሲፈፀምበት ለእረፍት ቤተሰቦቹ ጋር ለንደንን እየጎበኘ ነበር ተብሏል።

ቤተሰቦቹ "በልጃችን ላይ ለውጥ እያየን ነው። ቢያንስ አሁን ያለምንም ድጋፍ በእግሮቹ መቆም ችሏል" ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የማስታወስ ችሎታውም ቀስ በቀስ እየተሻሸለ ሲሆን በአንድ ቀን ውስጥ የሰራቸውን ወይም ከአንድ ቀን በፊት ያደረጋቸውን ማስታወስ መቻሉን ቤተሰቦቹ ተናግረዋል።

"አሁን ላይ ምግብም ራሱ መመገብ ችሏል፤ ወፈር ያሉ ፈሳሾችን መጠጣትም ጀምሯል ፤ በጣም ደስ የሚልና ወሳኝ ለውጦችን ማየት ችለናል" ብለዋል ቤተሰቦቹ።

ለታዳጊው ሕክምና የሚውል ከ250 ሺህ ፓውንድ በላይ ገንዘብ ተሰብስቦለታል።