ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰብዓዊ መብት፡በኢራቅና ሶሪያ ምዕራባዊያን ታጋቾችን በስለት የቀሉት በሞት አይቀጡም
የኢስላሚክ ስቴት (IS) አሸባሪ ቡድን አባላት እንደነበሩ የተጠረጠሩት ሁለቱ እንግሊዛዊያን በሞት እንደማይቀጡ አሜሪካ ለዩናይትድ ኪንግደም አረጋገጠችላት፡፡
ሁለቱ እንግሊዛዊያን ‹‹ዘ ቢትልስ›› በሚል ቅጽል ስም ነው በይበልጥ የሚታወቁት፡፡ ይህ ቅጽል ስም የተሰጣቸው የአነጋገር ዘዬያቸው የብሪቲሽ በመሆኑ ነው፡፡
አሜሪካ ለዩናይትድ ኪንግደም በደብዳቤ እንዳረጋገጠችው ሁለቱ ተጠርጣሪ አሸባሪዎች በሶሪያና በኢራቅ ሳሉ የምዕራብ አገር ዜጋ ታጋቾችን በቪዲዮ እየቀረጹ በመቅላት ቢጠረጠሩም ሞት አይፈረድባቸውም፡፡
አሌክሳንደር ኮቴይ እና አልሻፊ ኤልሼክ በሚል ስም የሚታወቁት እነዚህ ተጠርጣሪዎች በአሜሪካ እጅ ያሉ ፍርድ ጉዳያቸው ያለየላቸው የመጨረሻዎቹ የአይኤስ አባላት ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
አሜሪካ በነዚህ የቀድሞ የእንግሊዝ ዜጎችና የአይኤስ አባላት ጉዳይ የዩናይትድ ኪንግደምን ድጋፍ ስትሻ ነበር፤ ሆኖም በሞት ይቀጡ ይሆናል ወይ የሚለው ሁለቱን አገሮች ሳያግባባ ቆይቶ ነበር፡፡
‹በነዚህ የቀድሞ ዜጎቼ ጉዳይ መረጃ ለአሜሪካ ባቀብል የሞት ፍርድ ይበየንባቸው ይሆን?› የሚለው ጉዳይ እንግሊዝን ሲያስጨንቃት ቆይቷል፡፡ የሁለቱን አገራት የመረጃ ትብብር ላይ ደንቃራ የሆነውም ይኸው ነበር፡፡
እንግሊዝ የሞት ፍርድ ለሚሰጥበት ጉዳይ ተባባሪ እንድትሆን ሕግ አይፈቅድላትም፡፡
አሜሪካ አሁን በመጨረሻ ለእንግሊዝ ግልጽ እንዳደረገችው ከሆነ ‹ዘ ቢትልስ› ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ እንኳ የሞት ፍርድ አይጸናባቸውም፡፡
የአሜሪካ አቃየ ሕግ ዊልያም ባር ለዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል በጻፉላቸው ደብዳቤ ነው ይህን ያረጋገጡት፡፡
‹‹የአሜሪካ መንግሥት በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ የሞት ፍርድ እንዲሰጥ አይጠይቀም፣ እንደዚያ ቢፈረድባቸውም እንኳ ተፈጻሚ አይሆንም›› ይላል ደብዳቤው፡፡
ይህንን የዊሊያም ባርን ደብዳቤ እንደ ማረጋገጫ በመውሰድ እንግሊዝ ስለነዚህ ተጠርጣሪ ሁለት የአይኤስ አባላት የቀድሞ ዜጎቿ ለአሜረካ ወሳኝ የሚባል መረጃን ታቀብላለች፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች አሁን የሚገኙት በኢራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ ማቆያ ውስጥ ነው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የብሪታኒያ ዜግነት የነበራቸው ቢሆንም እንግሊዝ ዜግነታቸውን ሽራዋለች፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በአይ ኤስ ውስጥ የነበራቸው ሚና ምዕራባዊያንን እየጠለፉ በማገት በቪዲዮ እየቀረጹ መቅላት ነበር ተብሏል፡፡
በዚህ መንገድ አሰቃቂ ወንጀል ፈጽመውባቸዋል ከሚባሉት ውስጥ በ2014 ዓ.ም የተገደሉት አሜሪካዊያን ጋዜጠኞችና አንድ የእንግሊዝ የእርዳታ ሰራተኛ ይገኙበታል፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመባቸው ምዕራባዊያን በስለት አንገታቸው ሲቀላ በቪዲዮ ተቀርጾ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች እንዲሰራጭ ሆኗል፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም ሁለቱ የቀድሞ ዜጎቿ ተላልፈው እንዲሰጧት መጠየቅ ሕግ አይፈቅድላትም፡፡
በመሆኑም አሜሪካ እንግሊዝን ስለ ሁለቱ ሰዎች ጠቃሚ መረጃ እንድታቀብላት በጠየቀቻት ጊዜ ይህንኑ ለማድረግ ተስማምታ የሞት ፍርድ ቢሰጣቸውም እንደማትቃወም ገልጻ ነበር፤ መጀመርያ፡፡
ሆኖም ኋላ ላይ ይህ በአሜሪካና በዩናይትድ ኪንግደም መካከል የነበረው የትብብር መንፈስ እክል ገጥሞታል፡፡ ምክንያቱም የአንደኛው ተጠርጣሪ ኤልሻፊ ኤል ሼክ እናት የእንግሊዝ መንግሥትን በመክሰሷ ነው፡፡
ክሱም መሰረት ያደረገው ዩናይትድ ኪንግደም በዓለም ላይ የሞት ቅጣት እንዲወገድ የምትሰራ አገር ሆና ሳለ የቀድሞ ዜጎቿን በሞት እንዲቀጡ የሚያስችል መረጃ ማቀበሏ ትክክል አይደለም፣ ከዩናይትድ ኪንግደም መርህ እና እሴት ጋር ይቃረናል በሚል ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ዩናይትድ ኪንግደም አሜሪካ ሁለቱን የቀድሞ ዜጎቿን በሞት እንደማትቀጣቸው ማረጋገጫ እንድትሰጣት ለመጠየቅ ተገዳለች፡፡
በሁለቱ ተጠርጣሪ የአይኤስ አባላት ምክንያት ዘመድ ቤተሰቦቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተቀሉባቸው ምዕራባዊያን ‹‹ዘቢትልስ›› በሞት እንዲቀጡ እንደማይሹ ከዚያ ይልቅ ፍትሐዊ ፍርድ እንዲሰጥላቸው አጥብቀው መጠየቃቸውም እንግሊዝ ጥብቅ መረጃዎችን ለአሜሪካ አሳልፋ እንድትሰጥ ሳያበረታታት አልቀረም፡፡