አውስትራሊያ፡ ሻርክ በቡጢ በመምታት ሚስቱን ያተረፈው ግለሰብ

በአውስትራሊያ የሚገኝ ሻርክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አውስትራሊያ ውስጥ አንድ የውቅያኖስ ቀዛፊ ሻርክ በቡጢ ነርቷል። ከአንድም ሁለት ሶስቴ።

ሰውዬው የውቅያኖስ ማዕበልን የሚቀዝፍ [ሰርፈር] ነው። ታድያ ከዕለታት ባንዱ ከሚስቱ ጋር እየቀዘፈ ሳለ አንድ ሻርክ ይጠጋቸዋል። ሻርኩም ጊዜ ሳያጠፋ የሚስቱን ቀኝ እግር በስል ጥርሶቹ ይነክሳል።

ይህን የተመለከተው ባል ዘሎ ሻርኩ ላይ በመውጣት ሻርኩን በቡጢ 'እንካ ቅመስ' ይለዋል።

የ35 ዓመቱ ሻንቴል ዶይል ሻርኩ በጥርሶቹ የያዘውን የሚስቱን እግር እስኪለቅ ድረስ በቡጢ ነርቶታል ሲሉ የአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የሰውዬውን ቡጢ መታገስ ያልቻለው ሻርክ የነከሰውን እግር ለቆ እግሬ አውጭኝ ይላል። ሰውዬውም ሚስቱን ተሸክሞ ወደ ውቅያኖሱ ዳርቻ ይቀዝፋል።

ይህ ፊልም መሰል ክስተት የተከሰተው በአውስታራሊያዋ ኒው ሳውዝ ዌልስ ነው።

ቀኝ እግሯን በሻርክ የተነከሰችው ዶይል ክፉኛ ጉዳት ስለደረሰባት ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች።

የአካባቢው ባለሥልጣናት፤ ዶይል ሶስት ሜትር ርዝማኔ ባለው አንድ ታዳጊ ነጭ ሻርክ ነው የተነከሰችው ይላሉ።

ከሻርክ ጋር ቡጢ ገጥሞ የሚስቱን ሕይወት ያዳነው ግለሰብ በአውስትራሊያውን ዘንድ እየተሞገሰ ነው።

በውቅያኖስ የተከበበችው አውስትራሊያ ዜጎች ከሻርክ ጋር ትግል ሲገጥሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በዚሁ በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ብቻ ሻርክ የሰው ልጅ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በያዝነው ወር ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ውቅያኖስ በሚተፋው ማዕበል ታግዞ በዝርግ ሰሃን መንሸራተት [ሰርፊንግ] አውስትራሊያ ውስጥ እንደ ባሕል ስፖርት የሚቆጠር እንቅስቃሴ ሲሆን ብዙዎች በዚህ ስፖርት ምክንያት የሻርክ ሰለባ ይሆናሉ።