ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ለለውጥ ጎዳና ላይ ወጡ
በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ፖለቲካዊ ለውጥን በመሻት በተለያዩ ከተሞች ጎዳናዎች ለተቃውሞ ወጥተዋል።
ባለፈው አመት የሱዳኑን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን መገርሰስ ተከትሎ ቃል የተገቡ ማሻሻያዎችና ለውጦች ምን ላይ እንደደረሱ ተቃዋሚዎች በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
በመዲናዋ ኻርቱምን ጨምሮ በአጎራባች ከተሞችና ወደ ጦር ኃይሉ ዋና መቀመጫ የሚያመሩ ጎዳናዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተዋል።
ተቃዋሚዎችም የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ እንዲሁም በዘፈኖች፣ የመኪና ጥሩምባ በማሰማት ተቃውሟቸውን እየገለፁ ነው።
በአሁኑ ሰዓት እየተደረጉ ያሉ ተቃውሞዎች ባለፈው አመት ከነበረው፣ ለወራት ከዘለቀውና የኦማር አልበሽርን ረዥም የስልጣን ዘመን ማብቂያ ከሆነው አብዮትም ጋር ይመሳሰላል ተብሏል።
የኦማር አልበሽር ከስልጣን መውደቅ ተከትሎም የሲቪልና ወታደራዊ ጥምር መንግሥት ተመስርቷል።
ነገር ግን እውነተኛ የሲቪል መንግሥት እንዲሁም ፖለቲካዊ ለውጦች ይመጣሉ ወይ ለሚለው በርካቶች ስጋት አጭሮባቸዋል።
በትናንትናው ዕለት በተደረጉ ተቃውሞችም የተንሰራፋው ሙስና እንዲጠፋ፣ በአልበሽር አገዛዝ ወቅት የተገደሉ ሰዎች ፍትህ እንዲያገኙ እንዲሁም ቃል የተገባው ፓርላማ እንዲመሰረት የሚጠይቁ ነበሩ።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክም በበኩላቸው ቁልፍ የሚባሉ ማሻሻያዎችና ለውጦች በሃገሪቱ እንደሚካሄዱ ጠቅሰው በመጪዎቹ ቀናቶችም ይፋ ይሆናሉ ብለዋል።
ሃገሪቱ በተፈጠረው የገበያ ግሽበት ምክንያት የምግብ እንዲሁም የነዳጅ ዋጋ መጨመር ጫናን ፈጥሮባታል።
ከዚህም በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ቀጥ ማለትም ድቀትን እንዳይፈጥር ፍራቻን ደቅኗል።