የ'ሚሽን ኢምፖሲብል' ፊልም ቀረፃ በኮሮናቫይረስ ስጋት ተቋረጠ

ታትሟል

ታዋቂው ቶም ክሩዝ የሚተውንበት 'ሚሽን ኢምፖስኢብል' ፊልም ቀረፃ በኮሮናቫይረስ ስጋት ተቋርጠ።

'ኢምፖሲብል' የሚል ስያሜ የተሰጠው የፊልሙ ሰባተኛ ክፍል ቀረፃ ጣልያን ውስጥ ሲካሄድ ነበር። ነገር ግን ጣልያን በኮሮና መጠቃቷን ተከትሎ ዳይሬክተሩ 'ከት' ብለዋል።

ፓራማውንት የተሰኘው ግዙፍ የፊልም አምራች ኩባንያ ቬኒስ በተሰኘችው የጣልያን ከተማ ፊልሙን ለመቅረፅ ጓዙን ሸክፎ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ምክንያት ጉዞውን ሊሰርዝ ተገዷል።

ጣልያን ከ300 በላይ ሰዎች በኮሮና ተይዘውብኛል ስትል አሳውቃለች። ከእነዚህ መካከል 11 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ጣልያን በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት መካከል አንዷ ነች።

ምንም እንኳ የፊልሙ መሪ ተዋናይ ቶም ክሩዝ ቢሆንም ወደ ጣልያን አላመራም ነበር ተብሏል። ቀድመው ጣልያን ገብተው ካሜራ ሲደቅኑ የነበሩ ባለሙያዎች በመጡበት እግራቸው እንዲመለሱ ታዘዋል።

ፓራማውንት የተሰኘው ኩባንያ ምንም ቢሆን ከሠራተኞቼ ሕይወት አይበልጥም ሲል መግለጫ አውጥቷል። ባለሙያዎቹ ቫይረሱ ቀለል እስኪል ድረስ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ድርጅቱ አዟል።

'ሚሽን ኢምፖሲብል' ፊለም ከዚህ በፊት በነበሩት ቀረፃዎቹም ጣጣ አልተለየውም።

ለምሳሌ ሶስተኛው ክፍል ተሠርቶ ከወጣ በኋላ ማስታወቂያውን እንዲለፍፉ መንገድ ላይ የቆሙ መኪናዎችን ሰው በማስደንገጣቸው ፖሊስ ጣልቃ እንዲገባ ሆኖ ነበር።

በሌላ ወቅት ደግሞ ፕራግ ውስጥ ቀረፃ ለማድረግና ለቦታው 2 ሺህ ዩሮ ለመክፈል ከአሜሪካ ድረስ የመጡት ባለሙያዎች ዋጋው 2 ሺህ ሳይሆን 23 ሺህ ዩሮ ነው ተብለው የዜና ሲሳይ ሆነው ነበር።

ቶም ክሩዝ ፊልሙ ላይ የሚታዩ በርካታ ትዕይንቶችን ራሱ ነው የሚተውነው። እንደ ሌሎች ተዋናዮች ምትክ ተዋናይ [ስታንት] አይጠቀመምም። በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ አካላዊ ጉዳት ይደርስበታል። ስስተኛውን ክፍል ሲቀረፅ ወድቆ ጉልበቱ ተጎድቶ እንደነበር አይዘነጋም።