ፖሊስ 'ሴት ስለመሆንሽ ልብስሽን አውልቂና አረጋግጪልን'አለኝ

በኬንያ በአውቶቡስ ረዳትነት የምትሰራውና በተፈጥሮ ምክንያት ጺም ማብቀል የቻለችው ቴሬሳ ሙምቢ ብዙ ሰዎች ሴት ስለመሆኗ ለማመን ይቸገራሉ።
በአንድ ወቅት እስር ቤት ሳለች ፖሊስ ሴት ስለመሆኗ ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ልብሷን አውልቃ ይህንኑ እንድታረጋግጥ አስገድዷት ነበር።
ቴሬሳ ሙምቢ ለቢቢሲ ስዋሂሊ ባልደረቦቻችን እንደተናገረችው በናይሮቢ ትራፊክ ፖሊስ ይዟት እስር ቤት አስገብቷት ነበር። የገባችበት እስር ቤት ክፍል የሴቶች ነበር።
ከዚያም ሁለት የፖሊስ መኮንኖች መጥተው "አንተ ደሞ እዚህ ምን ትሰራለህ? በማለት ምርመራ አደረጉብኝ፤ ልብሴንም አስወለቁኝ" ብላለች።
ይህ የሆነው በፈረንጆች በሐምሌ 2018 ነው። ሆኖም ሙምቢ ልብሷን እንድታወልቅ የተገደደችበትን ዕለት እንደማትዘነጋው ትናገራለች።
ይህ አጋጣሚ ሙምቢ ከአውቶቡስ ረዳትነት ጎን ለጎን የሴቶች መብት ተሟጋች እንዳደረጋትና ሴቶች በማንኛውም መንገድ ጥቃት ሲደርስባቸው ወጥተው እንዲናገሩ ማበረታታት መጀመሯን ተናግራለች።
ሙምቢ የሆርሞን መዛባት የሚያመጣው የሕክምና እክል ተጠቂ በመሆኗ ነው የፊት ገጽታዋ ላይ ጢም ልታበቅል የቻለችው።
ወጣት ሳለች ጢሟን ሙልጭ አድርጋ በመላጨት ጊዜዋን ታጠፋ ነበር። 'ቆዳዬ እስኪላጥ ነበር የምላጨው' ትላለች ያን ዘመን መለስ ብላ በማስታወስ።
'ከሆነ ዓመት በኋላ ግን በቃ እርግፍ አድርጌ ተውኩት፤ ብጉር እየወጣብኝ፣ ቆዳዬም እያሳከከኝ ተቸገርኩና ጢሜን መላጨቱን እርግፍ አድርጌ ተውኩት' ትላለች።
ጢማም መሆን እያሳፈራት ከቤት መውጣት የተወችበት ጊዜም ነበር። 'ሱቅ ምናምን ማታ ማታ ብቻ መሄድ ጀምሬ ነበር' ትላለች።
ኑሮ እየከበዳት ሲመጣ ግን ቤት እየዋሉ የለት ጉርስ ማግኘት ከበዳት። የአውቶቡስ ረዳትም ሆነች።
በረዳትነት ላይ ሳለች ታዲያ እንደሷ ጢም ያበቀለች ሴት አጋጥማት እንደምታውቅና እንዳበረታታቻት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሙምቢ አሁን ጢማም ሴቶች ያቋቋሙት የኬንያ ማህበር አባል ስትሆን በነዚህ ስብሰባዎች በመገኘት ወጣት ሴቶችን ታበረታታለች።












