ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀሙት አርጀንቲናዊያን ቄሶች ዘብጥያ ወረዱ

ሕፃናትን ላይ ወሲባዊ ጥቃት የፈፀሙት ቄሶች ዘብጥያ ወረዱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአርጀንቲና ፍርድ ቤት ሁለት የሮማን ካቶሊክ ቤ/ክ ቄሶች መስማት የተሳናቸው ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅመዋል በማለት ከአርባ ዓመት በላይ እሥር በይኖባቸዋል።

ሆራሺዮ ኮርባቾ እና ኒኮላ ኮራዲ የተሰኙት ቄሶች እንዲሁም አንድ አትክልተኛ፤ እንደ ግሮጎሪ አቆጣጠር ከ2004-16 ባለው ጊዜ በአስገድዶ መድፈርና በሌሎች ወሲባዊ ጥቃቶች ሕፃናቱን አጎሳቁለዋል ተብሏል።

የቄሶች ሰለባ የሆኑ በርካታ ሰዎች የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ችሎት ተገኝተው ነበር።

የሮማ ካቶሊክ ቤ/ክ እናት ሃገር የሆነችው አርጂንቲናን የናጠው ይህ ዜና ሰዎች የወቀሳ ጣታቸውን ቤተክርስቲያኒቱ ላይ እንዲቀስሩ አድርጓል።

ብዙዎች ካቶሊክ ቤ/ክ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ተስኗት ነበር ሲሉ ይወቅሳሉ።

ሰኞ ዕለት ሜንዶዛ በተባለች የአርጀንቲና ግዛት የዋለው ችሎት ኮርባቾ የተባሉት የ59 ዓመት ቄስ በ45 ዓመት እሥር እንዲቀጡ ወስኗል።

የጣልያኗ ከተማ ቬሮና ለትምህርት እያሉ በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው ነገር ግን ክስ ሳይመሠርትባቸው የቀረው የ83 ዓመቱ ኮራዲ የተባሉት ቄስ ደግሞ 42 ዓመታት ተበይኖባቸዋል።

የቤተክርስቲያኒቱ ትምህርት ቤት አትክልተኛ አርማንዶ ጎሜዝ ደግሞ የ18 ዓመት እሥራቱን ተቀብሏል።

ወንጀለኞቹ ይግባኝ የማለት መብታቸውን እንዲነጠቁም ተደርጓል።

ብይኑ በሚነበብት ወቅት ችሎት ተገኝተው የነበሩ የቄሶቹ ሰለባ እናቶች ሲያነቡ ታይተዋል። ከችሎቱ ወጣ ብሎ ደግሞ ከፍተኛ ተቃውሞ ይሰማም ነበር።

ወሲባዊ ጥቃቱ እንዴት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት መስማት የተሳናቸው ወጣቶች [ወንጀሉ ሲፈፅምባቸው ሕፃናት ነበሩ] በደላቸውን እንደይናገሩ ማስፈራራት ይደርስባቸው እንደነበር መስክረዋል።

የሮማ ካቶሊክ ቤ/ክ ቄሶች ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅመዋል ተብለው ሲወቀሱም ሆነ ሲከሰሱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ቤተክርስቲያኒቱም ፈጣን ምላሽ አትሰጥም ተብላ ትብጠለጠላለች።

አርጀንቲናውያን፤ የቤተክርስያኗስ ይቅር ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ይሄ ሁሉ ሲፈፀም የት ነበሩ በማለት አሁንም ይጠይቃሉ።