በኬንያ በደረሰ የመሬት መንሸራተት 24 ሰዎች ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በኬንያ ምዕራብ ፖኮት በጣለ ከባድ ዝናብ ሳቢያ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት 24 ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።

የአካባቢው ባለስልጣናት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደተናገሩት፤ እስካሁን ድረስ የ12 ሰዎችን አስክሬን ያገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰባቱ ሕጻናት ናቸው ተብሏል።

የመሬት መንሸራተቱ የደረሰው ኚያርኩሊያን እና ፓሩአ በተሰኙ መንደሮች ሲሆን በአካባቢው ከባድ ዝናብ ሲጥል ነበር።

እንደ አካባቢው ባለስልጣናት ገለጻ ከሆነ መንደሮቹን የሚያገናኘው መንገድ በከባድ ጎርፍ ምክንያት የተቆረጠ ሲሆን አንድ ድልድይም መወሰዱን ገልጸዋል።

ጆዬል ቡላል የተሰኙ የአካባቢው ባለስልጣን ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም የጠፉ ሰዎችን የማፈላለግ ሥራ ላይ ማተኮራቸውን ተናግረዋል።

የግዛቲቱ ኮሚሽነር አፖሎ ኦኬሎ በበኩላቸው፤ መውጪያ ያጡ ሰዎችን ለመፈለግ ቢንቀሳቀሱም የአየር ጠባዩ አስቸጋሪ በመሆኑ ጥረታቸው ተደናቅፏል።

"ድልድዩ በጎርፍ የተወሰደበት አካባቢ ለመሄድ ሞክረን ነበር። አሁንም ድረስ እየዘነበ ነው" ማለታቸውን ስታንደርድ ኒውስ በድረ ገጹ ላይ አስነብቧል።

የኬንያ ቀይ መስቀል በበኩሉ በትዊተር ገጹ ላይ የመሬት መንሸራተት መከሰቱን አረጋግጦ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን እያደረገ መሆኑን ገልጧል።