ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የዝነኛው አርቲስት የሙዚቃ ድግስ ተሰረዘ
ታትሟል
ዝነኛው ታንዛኒያዊ ሙዚቀኛ ዳይመንድ ፕላተነምዝ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አደራሽ ሊያደርግ የነበረው የሙዚቃ ድግስ በጸጥታ ስጋት ምክንያት መሰረዙን አርቲስቱ አስታወቀ።
የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 22 ሊካሄድ በነበረው ኮንስርት ላይ ከዳይመንድ በተጨማሪ ሌለኛው ታንዛኒያዊ ሙዚቀኛ ሬቫኒ ተሳታፊ ነበር።
በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ በሲቪል እና የጦር ጄነራሎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ለሙዚቃ ዝግጅቱ መሰረዝ ምክንያት መሆኑ ታውቋል።
ነሲቡ አብዱል ጁማ ወይም በመድረክ ስሙ በስፋት የሚታወቀው ዳይመንድ ፕላተነምዝ፤ ከደቡብ አፍሪካው ቻናል ኦ የሙዚቃ ጣቢያ እና ከሂፒፖ ሙዚክ አዋርድ በርካታ ሽልማቶችን የተቀበለ ዕውቅ አቀንቃኝ ነው።
አርቲስቱ በኢንስታግራም ገጹ ላይ ''በኢትዮጵያ በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት ምክንያት የሙዚቃ ድግሱ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል። በክስቱት ለተጎዱት ቤተሰቦች እና ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ'' በማለተ ወደፊት ኮንስርቱ መቼ እንደሚካሄድ እንደሚያሳውቁ አስፍሯል።
ከ300-800 ብር ያስከፍል የነበረው የሙዚቃ ድግስ ላይ ያሬድ ነጉን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን አርቲስቶችም ተሳታፊ እንደነበሩ ማወቅ ተችሏል።
አምስት ነጥቦች ስለ ዳይመንድ ፕላትነምዝ
- በምስራቅ አፍሪካ ከባለ ብዙ ጸጋ ሙዚቀኞች መካከል ቀዳሚው ነው
- ዝነኛ ከመሆኑ በፊት የሰልባጅ ልብሶች ነጋዴ ነበር
- የግሉ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያ አለው
- ''ቦንግ ፈላቭ'' የተሰኘ የታንዛኒያ ሂፕ ሃፕ ዝነኛ አድርጓል
- በኢንስታግራም ገጹ 7 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት