ካናዳ ዜጎቿ ሽጉጥ ገዝተው እንዳይታጠቁ ልትከለክል ነው

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ አነስተኛ የእጅ ሽጉጥ መግዛትም ሆነ መታጠቅ እንዲከለከል ጠየቁ።

የትሩዶ መንግሥት በጠቅላላው የእጅ ሽጉጥ መግዛትም ሆነ ቤት ማስቀመጥ በሕግ እንዲያስቀጣ ረቂቅ እያወጣ ነው።

ረቂቁ እንደሚለው ካናዳዊያን የእጅ ሽጉጦቻቸውን ባይነጠቁም ከዚህ በኋላ አዲስ መግዛት ግን አይችሉም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሐሳብ ያፈለቁት በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት አንድ አፍላ ታጣቂ 19 ሕፃናትን ተኩሶ ከገደለ በኋላ ነው።

ሰኞ ዕለት ለካናዳ እንደራሴዎች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ የእጅ ሽጉጥ መግዛት፣ መሸጥ፣ ማዘዋወር አሊያም ወደ ካናዳ ማስገባትን ሙሉ በሙሉ የሚያግድ ነው።

"ለስፖርትና ለአደን ካልሆነ በቀር ካናዳዊያን በዕለተ ዕለት ኑሯቸው ሽጉጥ የሚታጠቁበት ምክንያት አይታየኝም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

"በጦር መሣሪያ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየጨመሩ ስናይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ግዴታችን ነው።"

ረቂቁ ከዚህም አልፎ የጦር መሣሪያ ካርታዎች ከአምስት በላይ ቀለሃ እንዳይዙ መደረግ እንዳለባቸው ያትታል።

የቤት ውስጥ ጥቃት የፈፀሙ አሊያም የትንኮሳ ወንጀል መዝገብ ያለባቸው ሰዎች ሽጉጣቸውን እንዲነጠቁም ሕጉ ሐሳብ አቅርቧል።

ምንም እንኳ ከአሜሪካ በተቃራኒው የጦር መሣሪያ መያዝ በሕገ-መንግሥቱ ተቀባይነት ባይኖረውም በካናዳ ገጠራማ ሥፍራዎች ሽጉጥ መታጠቅ ባሕል ሆኗል።

ካናዳ ሽጉጥ መግዛትና መታጠቅን በተመለከተ ጠበቅ ያለ ሕግ ያላት ሲሆን በጦር መሣሪያ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እምብዛም ናቸው።

ለምሳሌ ማንኛውም የጦር መሣሪያ ያለው ሰው ሳያቀባብል የተቆለፈ ቦታ እንዲያስቀምጥ ይገደዳል።

አልፎም የጦር መሣሪያ መግዛት የሚሻ ሰው ከባድ የሚባል ሂደት አልፎ ነው ምንሽር የሚታጠቀው።

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በደተጋጋሚ የተስተዋለውን የጦር መሣሪያ ጥቃት ተከትሎ ሕጉ ጠበቅ እንዲል ብዙዎች ሲወተውቱ ነበር።

በካናዳ ታሪክ እጅግ ብዙ ሰው አለቀበት በተባለለት ክስተት አንድ ጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በፈረንጆቹ 2020 ኖቫ ስኮሺያ በተባለች ከተማ 22 ሰዎችን መግደሉ የሚዘነጋ አይደለም።

ይህ በሆነ በቀናት ልዩነት ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ 1500 በሚሆኑ የጦር መሣሪያዎች ላይ እገዳ ጥለው ነበር።

አዲሱ ሕግ ተግባራዊ ከሆነ ካናዳዊያን ከዚህ በኋላ የጦር መሣሪያ የመግዛት ዕድላቸው ይመነምናል ማለት ነው።